የሮማው ተከላካይ ክሪስ ስሞሊንግ እና ቤተሰቡ በቤታቸው እንዳሉ በታጣቂዎች ተዘረፉ
የተፈጠረውን ነገር ለመለየት ፖሊስ አሁን ላይ የቪዲዮ ክትትል ካሜራዎችን በመመርመር ላይ ነው
ዘራፊዎቹ የስሞሊንግን እና የቤተሰቦቹን ውድ ሰዓቶች ፣ ጌጣጌጦችና ገንዘባቸውን መዝረፋቸው ተገልጿል
የቀድሞው የማንችስተር ዩናይትድ እና የአሁኑ የሮማው ተከላካይ ክሪስ ስሞሊንግ ፣ ከነቤተሰቦቹ በደቡብ ሮማ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው እንዳሉ ዘረፋ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ዛሬ አርብ ማለዳ ላይ ጠመንጃ ባነገቡ ግለሰቦች መዘረፋቸውን ከጣሊያን የወጡ ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡
በቁጥር ሦስት እንደሆኑ የተገለጹት ዘራፊዎቹ ፣ በመኝታ ክፍል መስኮት እንደገቡ ነው ዘገባዎች ያመለከቱት፡፡ እነዚህ ዘራፊዎች ታዲያ ፣ በታጠቁት ጠመንጃ በማስፈራራት የስሞሊንግን እና የቤተሰቦቹን ውድ ሰዓቶች ፣ ጌጣጌጦችና ገንዘባቸውን ዘርፈዋል፡፡
የጣሊያኑ የዜና ወኪል አንሳ እንደዘገበው ፣ ሶስቱ ዘራፊዎች የተጫዋቹ መኝታ ክፍል መስኮት ላይ ያለውን ፍርግርግ ካስወገዱ በኋላ ነው ከዋና ከተማው ወጣ ብሎ በአፒያ መንገድ አካባቢ ወደሚገኘው ወደ ተጫዋቹ ቤት የገቡት፡፡
ከዚያም በጠመንጃ በማስፈራራት ውድ እቃዎች የሚገኙበትን ሳጥን እንዲከፍት አስገድደውት ፣ ሶስት የሮሌክስ ሰዓቶችን ፣ ጌጣጌጦችንና 300 ዩሮ የሚሆን ጥሬ ገንዘብ ወስደው ማምለጣቸው ተዘግቧል፡፡
በዘረፋው ወቅት የስሞሊንግ ቤተሰቦችም በቤት ውስጥ የነበሩ ሲሆን ፣ ከዘረፋው በኋላ የስሞሊንግ ባለቤት ከጠዋቱ 5 ሰዓት አካባቢ ለፖሊስ ደውላለች፡፡
የተፈጠረውን ነገር ለመለየት ፖሊስ አሁን ላይ የቪዲዮ ክትትል ካሜራዎችን እየመረመረ ነው ተብሏል፡፡
ስሞሊንግ እና ክለቡ ሮማ ስለሁኔታው እስካሁን ምንም አስተያየት አልሰጡም፡፡ ነገር ግን የቀድሞው የማንችስተር ዩናይትድ የቡድን አጋር ማርከስ ራሽፎርድ በትዊተር ገፁ ሀዘኑን ገልጿል፡፡
በተመሳሳይ የሮማ አሰልጣኝ ፓውሎ ፎንሴካ እና ቤተሰቡ ከቤት ውጭ እያሉ ባለፈው ህዳር ወር ላይ ቤታቸው ተሰሮ ሰዓቶች እና ሌሎች ውድ ዕቃዎች ተወስደውባቸዋል፡፡
የላዚዮው የፊት ተሰላፊ የአኪን ኮሬያም ሮም የሚገኘው ቤቱ ከቀናት በፊት ተዘርፏል ፡፡