በቱርክ ለ8 ቀናት በፍርስራሽ ውስጥ የቆዩ ሰባት ሰዎች በህይወት ተገኙ
ይህም የነፍስ አድን ስራውን ሙሉ በሙሉ ተሰፋ የሚያቆርጥ እንዳልሆነ አሳይቷል
በቱርክ የደረሰው ርዕደ መሬት ያደረሰው ጉዳት ከ1939ኙ ተመሳሳይ አደጋ የከፋ ነው ተብሏል
በቱርክና ሶሪያ ከደረሰው አሳዛኝ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ማትረፍ ተችሏል።
እትብቷ ሳይቆረጥ ከቀናት በኋላ በፍርስራሽ ውስጥ የተገኘችውን ሶሪያዊ “አያ”ን ጨምሮ በርካታ ህጻናትና አዛውንቶች በተአምር ተርፈዋል።
በትናንትናው እለትም ከስምንት ቀናት በኋላ ሰባት ሰዎች ከነበሩበት ፍርስራሽ ውስጥ በነፍስ አድን ሰራተኞች እንዲወጡ መደረጉን አናዶሉ ዘግቧል።
በአስገራሚ ሁኔታ በህይወት ከተገኙት ውስጥ በሃታይ ግዛት በዩክሬናውያን የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ከፍርስራሽ ውስጥ የወጡት ይገኙበታል።
በደቡባዊ ቱርክ ሞሃመድ ካፈር የተባለ የ18 አመት ወጣትም አደጋው ከደረሰ ከ198 ስአታት በኋላ በህይወት ተገኝቷል።
ካፈር በፍጥነት ወደ አዲያማን ሆስፒታል ሲወሰድ የሚያሳዩ ምስሎችም ወጥተዋል።
በካህራማንማራስ ግዛትም ሁለት ወንድማማቾችን ዘግቶ አላሳልፍ ካላቸው ፍርስራሽ እንዲወጡ መደረጉም የነፍስ አድን ሰራተኞችን ማስደሰቱ ተነግሯል።
ከስምንት ቀናት በኋላ የሰባት ሰዎች ህይወትን ማትረፍ መቻሉም የነፍስ አድን ስራው ያለቀለትና ተስፋ የሚያስቆርጥ እንዳልሆነ ማመላከቱንም ነው ሬውተርስ የዘገበው።
በሬክተር ስኬል 7 ነጥብ 8 ሆኖ የተመዘገበው ርዕደ መሬት በቱርክና ሶሪያ ከ37 ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት ቀምቶ ሚሊየኖችን ማፈናቀሉን ደግሞ ቲ አር ቲ አስነብቧል።
በቱርክ ብቻ ከ35 ሺህ በላይ ሰዎችን የገደለው ርዕደ መሬት ቱርክ ከአንድ ምዕተ አመት በኋላ ያስተናገደችው ዘግኛኝ አደጋ መሆኑን ፕሬዝዳንት ሬስፕ ጣይብ ኤርዶሃን ተናግረዋል።
በፈረንጆቹ 1939 በኢርዚንካን በደረሰ መሰል አደጋ ከ33 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉንም በማስታወስ።
በጥር 29ኙ አደጋ የተመዘገበው የሟቾች ቁጥር አሁንም እንደሚያሻቅብ ይጠበቃል፤ ከ105 ሺህ በላይ ሰዎችን ያቆሰለው ርዕደ መሬት ዘርፈ ብዙ ቀውሱም ቀጥሏል።