በርዕደ መሬት ጉዳት ስለደረሰበት የቱርኩ “ጋዚያንቴፕ ቤተመንግስት” ምን ያውቃሉ ?
ቤተመንግስቱ ወታደራዊ ተልዕኮዎችን ለመፈጸም ምቹ ስፍራ እንደነበር ይነገራል
ከ2 ሺህ አመት በላይ እድሜ ያለው “ጋዚያንቴፕ ቤተመንግስት” ቱርክ ከምትመካባቸው መስህቦቿ አንዱ ነው
በቱርክ ያጋጠመው ከባድ ርዕደ መሬት ዘመናትን ባስቆጠረው የጋዚያንቴፕ ቤተመንግስት ላይም ጭምር ጉዳት አድርሷል፡፡
የቱርክ የባህል ሚኒስቴር የአርኪዮሎጂስቶች መረጃ ጠቅሶ እንደገለጸው ከሆነ ርዕደ መሬቱ ከተከሰተባት የጋዚያንፔት ከተማ 20 ማይል ርቀት ላይ ከፍ ባለ ስፍራ የሚገኘው የጋዚያንቴፕ ግንብ የመፈራረስ ጉዳት ደርሶበታል፡፡
የጋዚያንቴፕ ቤተ መንግስት ባለፉት መቶ አመታት ለወታደራዊ እና ሲቪል ስራዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ የነበረው ታሪካዊ ስፍራ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በተለይም በ20 ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ከፈረንሳይ ኃይሎች ጋር በተደረገው ጦርነት ቤተ መንግስቱ ወታደራዊ ተልዕኮዎችን ለመፈጸም ምቹ ስፍራ ሆኖ ማገልገሉ ነው የሚነገረው፡፡
በባይዛንታይን ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ጀስቲንያን የግዛት ዘመን እንደተገነባ የሚነገርለት ቤተ መንግስት፤ በሬክተር ስኬል 7.8 በተመዘገበው በአሁኑ አደጋ በርካታ የህንጻው ክፍሎች እንደተገዱበትም ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው፡፡
የቱርክ የዜና ወኪል አናዶሉ ያሰራጨው ምስል በኮረብታማ ስፍራ ላይ የሚገኘው ግንብ ሲፈራርስ ያሳያል፡፡
በተጨማሪም ከቤተ መንግስቱ አጠገብ ያለው ታሪካዊ መስጂድ ግንብ መፍረሱንም የሚያሳዩ ምስሎች ወጥተዋል።
“ከ 2200 አመታት በፊት የተገነባው የጋዚያንቴፕ ቤተመንግስት” ማራኪ የስነ-ህንጻ ጥበብ ውጤት መሆኑ ይነገርለታል፡፡
ቤተ መንግስቱ በጋዚያንቴፕ ከተማ መሃል ከ25-30 ሜትር ከፍታ ላይ በሚታየው ኮረብታ ላይ ይገኛል፡፡
ቤተ መንግስቱ በበርካታ አገዛዞችና ነገስታት እድሳት እና ጥገና ከተደረገለት በኋላ በ16ኛው ክፍለ ዘመን አሁን ያለበትን ይዘትና ቅርጽ ሊይዝ እንደቻለም ይነገራል፡፡
በዙሪያው 12 ማማዎች ያሉት ቤተ መንግስት ቱርክ ከምትመካባቸው ድንቅ መስህቦች አንዱ ነው፡፡