ለዘረኛ ስድብ ያልተሸነፈው ኢትዮ - አውስትራሊያዊ ኮሜዲያን ጆ ኋይት
ጆ ኋይት “ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ ግን አሁንም አልተራብኩም” በሚል ርዕስ በሚያቀርበው የመድረክ የኮሜዲ ስራ ይታወቃል
ከሰሞኑም ከአንድ ታዳሚ ለተሰነዘረበት የዘረኛ ስድብ የሰጠው ምላሽ የአውስትራሊያ መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ስቧል
ከኢትዮጵያውያን ቤተሰቦቹ በሱዳን በስደት ላይ ከነበሩ ቤተሰቦቹ የተወለደው ጥላሁን ሃይሉ ወይም ጆ ኋይት በአውስትራሊያ እውቅናን ያተረፈ ኮሜዲያን ነው።
ጥላሁን ከእናቱ እና አምስት እህቶቹ ጋር ለተሻለ ህይወት ወደ አውስትራሊያ ፐርዝ ከተማ ሲያቀና ገና በአስራዎቹ የሚገኝ ህጻን ነበር።
በትምህርት ቤት ኳስ ሲጫወቱ የቡድን አጋሮቹ ስሙን ለመጥራት ሲቸገሩ ስሙን ወደሚወደው የአር ኤንድ ቢ አቀንቃኝ “ጆ ኋይት” መለወጡንም ለኤን ቢ ሲ ይናገራል።
ጆ ኋይት ከልጅነቱ ጀምሮ በቤተሰቦቹ ጨዋታ አዋቂ እንደሆነ እየተነገረው ነው ያደገው።
“ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን ጦርነትን ሸሽተው የተሰደዱ ቤተሰቦቼ የኔ ቀልድ የስደት ፈተናዎቹን ማስረሻ አድርገውት እንደነበር ይነግሩኛል” የሚለው ጥላሁን፥ ይህ የቤተሰቦቹ ማበረታቻም ወደ ኮሜዲ ስራ እንዲሳብ እንዳደረገው ይናገራል።
የእንግሊዝኛ ቁንቋ ክህሎቱን በአጭር ጊዜ ያሳደገው ጥላሁን ሃይሉ ወይም ጆ ኋይት፥ በባንክ ዘርፍ ትምህርቱን አጠናቆ ስራ ቢጀምርም ነፍስያው የወደደችው የኮሜዲ ስራን ነው።
እናም በፐርዝ እና ሌሎች ከተሞች እየተዘዋወረ የኮሜዲ ስራዎችን ማቅረብ መጀመሩን ያወሳል።
“ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ ግን አሁንም አልራበኝም” በሚል ርዕስ በተለያዩ ከተሞች ያቀረባቸው የመድረክ የኮሜዲ ስራዎችም ተቀባይነት ማግኘት ችለዋል።
የኮሜዲ ስራዎቹ በሱዳን ያሳለፈውን የስደት ህይወት፣ በአውስትራሊያም የገጠመውን አዳዲስ የባህልና ቋንቋ ፈተና የሚያሳዩና ለስደተኞች ብሩህ እይታ እንዲኖር በቀልድ እያዋዙ የሚጠይቁ ናቸው።
እናቱ እርሱን ጨምሮ ስድስት ልጆችን ለማሳደግ የከፈለችውን መስዋዕትነትም በቀልዶቹ ያነሳል።
በ2019 አፍሪካውያን ኮሜዲያኖችን አሰባስቦ በሜልቦርን እና ፐርዝ ተወዳጅነትን ያተረፈ የኮሜዲ ምሽት ያዘጋጀው ጆ ኋይት፥ አፍሪካውያን እምቅ ችሎታቸውን እንዲያወጡት መድረክ መፍጠር ይገባል ይላል።
በትልልቅ አለም አቀፍ መድረኮች ለአፍሪካውያን ኮሜዲያኖች በሮችን የሚዘጉት በርካታ በመሆናቸውም ለራሱም ሆነ ለሌሎች የሙያ አጋሮቹ እድል በመፍጠር ላይ ይገኛል።
በስራዎቹ ተወዳጅነት ምክንያት በአውስትራሊያ መገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ የቀረበው ጥላሁን ሃይሉ ወይም ጆ ኋይት፥ በሜልቦርን የአፍሪካውያን ኮሜዲያኖች ቡድን እንዲመሰረትም ትልቅ ድርሻ እንዳለው ኤን ቢ ሲ በዘገባው አስፍሯል።
ጆ ኋይት ከሰሞኑም በፐርዝ ከተማ “ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ ግን እስካሁን አልተራብኩም” በሚል ርዕስ የኮሜዲ ስራውን አቅርቧል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ታዳሚዎች እየተከታተሉት የነበረውን የመድረክ ስራ ግን አንድ ታዳሚ ሊያውከው መሞከሩን ዴይሊ ሜል አስነብቧል።
ከቆዳ ቀለሙ ጋር የተያያዘ ስድብን ደጋግሞ ሲሰድበውም መረበሹን ዋጥ አድርጎ ስራውን መቀጠሉን ኋይት በፌስቡክ ገጹ ላይ አጋርቷል።
ከዚህ ቀደምም የተለያየ ዘር ተኮር ስድብ እንደደረሰበት የሚያስታውሰው ኋይት፥ “በግልፍተኝነት መልስ ብሰጥ አክብረውኝ የመጡ ታዳሚዎቼን አስከፋለሁ ብዬ ስሜቴን ዋጥ አድርጌዋለሁ” ብሏል።
የኮሜዲ ስራው እንደተጠናቀቀም ተሳዳቢው ታዳሚ ወደ ኋይት በመምጣት አድናቆቱን ገልጾለት ይቅርታን ጠይቋል።
“ታዳሚው ዘር ተኮር ስድቡ ምን ያህል ሊረብሸኝ እንደሚችል በሚገባ አልተረዳም ነበር፤ ነግሬው አምኖበታል፤ ይቅርታም ጠይቆኝ ተጨባብጠን ተሰነባብተናል” ነው ያለው ጥላሁን ሃይሉ።
በፐርዝ ከተማ እንደ ጥላሁን ያሉ በርካታ ኮሜዲያኖች የተሰባሰቡበት የፊንጅ ወርልድ ፌስቲቫል መካሄዱን ቀጥሏል።
ከኢትዮጵያውያን ቤተሰቦቹ በሱዳን ተወልዶና አድጎ በአውስትራሊያ የኮሜዲ ስራ መንገስ የጀመረው ጥላሁን ሃይሉ ወይም ጆ ኋይትም በዚሁ መድረክ ተወዳጅ ስራውን እያቀረበ ይገኛል ብሏል የአውስትራሊያው ኤን ቢ ሲ።