ገናን ከኢትዮጵያ ጋር የሚያከብሩት ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ግብጽ፣ ሩስያ እና ዩክሬንን ጨምሮ 14 ሀገራት የገና በዓልን በዛሬው እለት እያከበሩ ነው
የጎርጎሮሳውያኑን የዘመን ቀመር የሚከተሉ ሀገራት ክርስቲያኖች የገና በዓልን ከቀናት በፊት ማክበራቸው ይታወሳል
ገናን ከኢትዮጵያ ጋር የሚያከብሩት ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ገና በምስራቅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ በዛሬው እለት እየተከበረ ነው።
ኢትዮጵያን ጨምሮ የጁሊያን የዘመን ቀመር የሚከተሉት ሀገራት ናቸው በተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ስነ ስርአቶች በዓሉን እያከበሩ የሚገኙት።
ከአለማችን ህዝብ 12 ከመቶው የኦርቶዶክስ ክርስቲያን መሆኑን ታይም መጽሄት ይዞት በወጣው መረጃ ያመላክታል።
ከ250 እስከ 300 ሚሊየን የሚደርሱ ሰዎች የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነትን እንደሚከተሉም ነው ግምቱን ያስቀመጠው።
በምስራቅ አውሮፓ፣ መከከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ ኢትዮጵያ እና ግብጽ ከፍተኛ የእምነቱ ተከታዮች ቁጥር ይገኝባቸዋል።
የዘመን ቀመሯን ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ጋር ያዋደደችው ኢትዮጵያ 2016ኛውን የልደት በዓል እያከበረች ነው።
በዓሉ በተለይም በላሊበላ የወትሮ ድምቀቱን ይዞ ተከብሯል።
ከ15 ሚሊየን በላይ የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ አማኞችም የገና በዓልን በዛሬው እለት እያከበሩት ነው።
ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ ኤል ሲሲም ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፥ ግብጻውያን ክርስቲያኖች ከክርስቶስ ሰላማዊነትን፣ መቻቻል፣ ይቅርታ እና ለጋስነትን ሊማሩ ይግባል ብለዋል።
በሩሲያም የገና በዓል ዋዜማን በጾም የሚያሳልፉ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በዛሬው እለት የገና በዓልን በማክበር ላይ ናቸው።
ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንም እንደወትሯቸው ህዝብ በተሰበሰበበት ባይሆንም በክሬምሊን በሚገኝ ካቴድራል የቅዳሴ ስርአት ላይ መገኘታቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን አስነብበዋል።
የዓለም ኦርቶዶክሳውያን የገና በዓልን እያከበሩ ነው
ፕሬዝዳንት ፑቲን በትናንትናው ዕለት ወይም በበዓሉ ዋዜማ ላይ በጦር ግንባር ለሚገኙ ሩሲያዊያን እንኳን አደረሳችሁ ብለው ለሀገራቸው እየከፈሉት ላለው ዋጋ መንግስታቸው እውቅና እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
ዩክሬናውያን የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የዘንድሮውን ገና ባሳለፍነው ሳምንት በይፋ ለመጀመሪያ ጊዜ ከእናቷ ሩሲያ ተነጥላ ከሌሎች የአውሮፓዊያን ጋር ያከበረች ቢሆንም ብዙ ዩክሬናዊያን የገናን በዓል እንደለመዱት ዛሬ ማክበራቸው ተሰምቷል፡፡
የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት በሚገኙባቸው ኤርትራ፣ እስራኤል፣ አርመኒያ፣ ሰርቢያ፣ ቤላሩስ፣ ሞንቴኔግሮ፣ ቡልጋሪያ፣ መቄዶኒያ፣ ጆርጂያ እና ሞልዶቫም የገና በዓል በዛሬው እለት እየተከበረ ነው።
የጎርጎሮሳውያኑን የዘመን ቀመር የሚከተሉ ክርስቲያኖች ከአንድ ሳምንት በፊት የገና በዓልን ማክበራቸው ይታወሳል።