የዓለም ኦርቶዶክሳውያን የገና በዓልን እያከበሩ ነው
በሩማኒያ፣ ቡልጋሪያ፣ ቆጵሮስ እና ግሪክ የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን በፈረንጆቹ ባሳለፍነው ታህሳስ 25 ነው በዓሉን ያከበሩት
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከሞስኮው ወጣ ብሎ በሚገኘው ኖቮ ኦጋርዮቮ ከተማ ተገኝተው በዓሉን አክብረዋል
በተለያዩ ክፍላተ ዓለማት የሚገኙ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ገናን እያከበሩ ነው፡፡
በኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማንያን ዘንድ በመከበር ላይ የሚገኘው የገና በዓል በሩሲያ፣ ሰርቢያ፣ ሩማኒያ፣ ቡልጋሪያ፣ ቆጵሮስ፣ ግሪክ እና በሌሎችም ሃገራት እየተከበረ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያኑን ጨምሮ አብዛኞቹ የዓለም ኦርቶዶክሳውያን ዛሬ ታህሳስ 29 ነው በዓሉን የሚያከብሩት፡፡ ሆኖም አንዳንድ ቀደም ብለው የሚያከብሩ ሃገራትም አሉ፡፡
በሩማኒያ፣ ቡልጋሪያ፣ ቆጵሮስ እና ግሪክ የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን በፈረንጆቹ ባሳለፍነው ታህሳስ 25 ነው በዓሉን በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስነ ስርዓቶች ያከበሩት፡፡
ኦርቶዶክሳውያኑ ሃገራትን ባዳረሰው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ውስጥ ሆነው ነው በዓሉን በማክበር ላይ ያሉት፡፡
ይህን ተከትሎም ሩሲያን ጨምሮ በተለያዩ ሃገራት የቁጥጥር መንግዶች በጥብቅ እንዲተገበሩ ታዟል፡፡ የፊትና የአፍ መሸፈኛዎች እንዲደረጉም ጥብቅ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከሞስኮው ወጣ ብሎ በሚገኘው ኖቮ ኦጋርዮቮ ከተማ ነው በዓሉን ያከበሩትና ኃይማኖታዊ ስነ ስርዓቶችን የታደሙት፡፡
የሰርብ ኦርቶዶክሶች በዋና ከተማቸው ቤልግሬድ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በመሰባሰብ በተለያዩ ስነ ስርዓቶች በዓሉን በማክበር ላይ ይገኛሉ፡፡
ከኮሮና የምርመራ እና የክትባቶች ሂደት ጋር በተያያዘ በአውስትራሊያ ኦፕን እንዳይሳተፍ የታገደው ቁጥር አንዱ የዓለም የሜዳ ቴኒስ ሻምፒዮና ኖቫክ ጆኮቪችም በሜልቦርን የስደተኞች ማቆያ እስር ቤት ውስጥ ሆኖ በዓሉን በማክበር ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡
ካዛኪስታናውያን ከሰሞኑ በሃገራቸው ከተቀሰቀሰው ከባድ አመጽ ጋር በተያያዘ በዓሉን ልክ እንደ ካሁን ቀደሙ ሁሉ እያከበሩ አይደለም፡፡ በመላ ሃገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ይታወሳል፡፡