የአሜሪካው ሲአይኤ በኮሮና ቫይረስ ጉዳይ ቻይና ሀላፊነት እንድትወስድ ጠየቀ
ኮሮና ቫይረስ በተፈጥሯዊ መንገድ ሳይሆን ከቤተ ሙከራ የተለቀቀ ቫይረስ መሆኑን አሜሪካ ትምናለች ተብሏል
አሜሪካ እንደ ሀገር ለ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎቿ ሞት ተጠያቂ አለማድረጓ እንደሚያስቆጭም ሲአይኤ ገልጿል
የአሜሪካው ሲአይኤ በኮሮና ቫይረስ ጉዳይ ቻይና ሀላፊነት እንድትወስድ ጠየቀ።
በሳይንሳዊ ስሙ ኮቪድ-19 በመባል የሚጠራው ገዳይ ወረርሽኝ የህዝብ አደጋ መሆኑ ካበቃ ሶስት ዓመታት አልፈዋል።
ቫይረሱ በመላው ዓለም 7 ሚሊዮን ዜጎችን እንደገደለ የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ያስረዳል።
ይሁንና በቫይረሱ የሞቱ ዜጎች ትክክለኛው ቁጥር 19 ሚሊዮን እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን አሀዙ እስካሁን እያጨቃጨቀ ይገኛል።
የመጀመሪያው የቫይረሱ ተጠቂ በቻይናዋ ሁናን ግዛት ዉሀን መገኘቱን ተከትሎ ቤጂንግ ቫይረሱ ላደረሰው ጉዳት ሀላፊነት እንድትወስድ አሜሪካ ደጋግማ ጠይቃለች።
ቫይረሱ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ አሜሪካዊያንን ገድሏል የተባለ ሲሆን ከ100 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ደግሞ አጥቅቷል።
አዲሱ የአሜሪካ ማዕከላዊ ስለላ ድርጅት ወይም ሲአይኤ ሀላፊ ጆን ራትክሊፍ እንዳሉት የኮሮና ቫይረስ በተፈጥራዊ መንገድ የተከሰተ ሳይሆን ከቤተ ሙከራ ያመለጠ የመሆን እድሉ ሰፊ መሆኑን ተናግረዋል።
ሀላፊው አክለውም ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ አሜሪካዊያን መሞት ምክንያት የሆነው ቫይረስ እንደ ሀገር እስካሁን ወጥ አቋም አለመያዙ ትክክል አለመሆኑንም ጠቅሰዋል።
ቻይና በበኩሏ ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ አምልጧል የሚለው አስተያየት አሜሪካ ቻይናን ለማጥቃት በሚል የምታሰራጨው መረጃ ነው በሚል ውድቅ አድርጋለች።
ዶናልድ ትራምፕ ኮሮና ቫይረስን በተደጋጋሚ "የቻይና ቫይረስ" እያሉ ሲጠሩ የሚሰሙ ሲሆን ቤጂንግ በአሜሪካ እና በመላው ዓለም ላይ ለደረሰው ጉዳት ካሳ ልትከፍል እንደሚገባም ተናግረዋል።
ኮሮና ቫይረስ ከእንስሳት ወደ ሰው እንደተላለፈ የተገለጸ ሲሆን የዓለም ጤና ድርጅት ስለ ቫይረሱ አመጣጥ ለማጥናት ያቀረባቸውን ጥያቄዎች ውድቅ ማድረጓ ይታወሳል።