የአሜሪካው የስለላ ድርጅት የቅጥር ማስታወቂያ አውጥቷል
ሲአይኤ ከቻይና፣ ሰሜን ኮሪያ እና ኢራን መረጃ የሚያቀብሉ ሰዎችን ለመቅጠር ነው ማስታወቂያውን በማህበራዊ ትስስር ገጾቹ ያወጣው
የስለላ ድርጅቱ ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት እንደጀመረች ሩሲያውያን መረጃ አቀባዮችን የመለመለበትን መንገድ “ስኬታማ” እንደነበር ገልጿል
የአሜሪካው የስለላ ድርጅት (ሲአይኤ) መረጃ አቀባዮችን ለመቅጠር ማስታወቂያ አውጥቷል።
ድርጅቱ በቻይና፣ ሰሜን ኮሪያ እና ኢራን የሚገኙ መረጃ አቀባዮችን መመልመል መጀምሩን ገልጿል።
ሲአይኤ በማንዳሪን፣ ፋርሲ እና ኮሪያኛ ቋንቋዎች በማህበራዊ ትስስር ገጾቹ በለጠፈው የቅጥር ማስታወቂያ አመልካቾች ደህንነታቸውን በጠበቀ መንገድ ስም፣ አድራሻ እና ዝርዝር መረጃቸውን እንዲልኩ ጠይቋል።
ያልተለመደው የቅጥር ማስታወቂያ የስለላ ድርጅቱ ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት እንደከፈተች ካወጣው መሰል ማስታወቂያ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የተለጠፈው።
ሩሲያውን መረጃ አቀባዮችን የተመለመለበት መንገድ “ስኬታማ” ነበር ያሉት የሲአይኤ ቃልአቀባይ፥ “አምባገነናዊ መንግስታት ባሉባቸው ሀገራት ለሚኖሩ ዜጎች ለቢዝነስ ክፍት መሆናችን ማሳወቅ እንወዳለን” ብለዋል።
በፌስቡክ፣ ኤክስ፣ ዩቲዩብ፣ ኢንስታግራም፣ ቴሌግራምና ሊንክዲን የተለጠፈው ማስታወቂያ አመልካቾች የሚገኙበትን ስፍራ የሚለውጡ መተግበሪያዎችን (ቪፒኤን) ተጠቅመው በሲአይኤ ይፋዊ ድረገጽ ማመልከት እንደሚችሉ አመላክቷል።
“መረጃ አቀባዮችን ለመመልመል በማህበራዊ ሚዲያዎች ማስታወቂያ ሲወጣ አላስታውስም” የሚሉት በሴኡል የሃንኩክ ዩኒቨርሲቲ የአለማቀፍ ፖለቲካ ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ማሶን ሪቺ፥ ሰሜን ኮሪያውያን የኢንተርኔት አገልግሎት በማያገኙበት ሁኔታ ምልመላው የመሳካት እድሉ ዝቅተኛ መሆኑን ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ የቅጥር ማስታወቂያው ወደ ቻይና በህገወጥ መንገድ የሚሻገሩና “ቪፒኤን” የሚጠቀሙ ሰሜን ኮሪያውያን ነጋዴዎች ላይ ያነጣጠረ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
አሜሪካ የመረጃ ቁጥጥሩ በሚጠነክርባቸውና የኢንተርኔት አገልግሎት በተገደበባቸው ሰሜን ኮሪያ፣ ቻይና እና ኢራን የስለላ መረጃዎችን መሰብሰብ እንደሚከብዳት የቢቢሲ ዘገባ ያሳያል።
የስለላ ድርጅቱ ሲአይኤም “የዜጎች መብት በሚረገጥባቸውና አፈና በበዛባቸው ሀገራት” መረጃ አቀባዮችን ለመመልመል ዘመኑ የሚጠይቀውን አካሄድ ለመከተል ጥረት እያደረገ መሆኑን ነው ባወጣው መግለጫ የጠቆመው።
በአሜሪካ የቻይና ኤምባሲ ቃልአቀባይ ሊዩ ፔንግዩ ዋሽንግተን በቻይና ላይ “የተቀናጀ የመረጃ ጦርነት አውጃለች” ሲሉ ወቅሰዋል።
“የቻይናን ህዝብ ከኮሚዩኒስት ፓርቲው ጋር ለመነጣጠል የሚደረግ ሙከራ በፍጹም የሚሳካ ጉዳይ አለመሆኑንም ሊረዱት ይገባል” ባይ ናቸው።
የሃንኩክ ዩኒቨርሲቲ የአለማቀፍ ፖለቲካ ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ማሶን ሪቺ በበኩላቸው የሲአይኤ የመረጃ አቀባዮች የቅጥር ማስታወቂያ አሜሪካ የተጋረጠባትን የደህንነት ስጋት የምትመለከትበትን መንገድ ያሳያል ብለዋል።
“አሜሪካ አሁን ላይ ከቻይና ወይም ከሩሲያ፣ ኢራን እና ሰሜን ኮሪያ ጋር የተናጠል ሰጣ ገባ ሳይሆን እየተመሰረተ ካለ ቡድን ጋር ነው ፍጥጫዋ፤ ይህንንም በደንብ የተረዳችው ይመስላል” ሲሉም ያክላሉ።
ይህንንም በመገንዘብ ይመስላል አሜሪካ ለሩሲያውያን ያወጣችውን የመረጃ አቀባዮች የቅጥር ማስታወቂያ ለቻይና፣ ሰሜን ኮሪያ እና ኢራንም የደገመችው።