የእስራኤል ሶስቱ ቁልፍ የስለላ ቡድኖች የትኞቹ ናቸው?
“ዩኒት 8200”፣ “ዩኒት 9900” እና “ዩኒት 504” የሄዝቦላህና ሃማስ መሪዎችን ለመግደል የተካሄዱ ሚስጢራዊ ዘመቻዎችን መርተዋል
ሶስቱ ቡድኖች ልዩ ተልዕኳቸውን በስኬት መወጣታቸው የእስራኤልን የስለላና የቴክኖሎጂ አቅም ለማሳየት አግዘዋል ተብሏል
እስራኤል የሄዝቦላህ እና ሃማስ መሪዎችን በተከታታይ ለመግደሏ የስለላ ተቋማቷ ጥንካሬ ማሳያ መሆኑ ይነገራል።
የሄዝቦላህ መሪ ሀሰን ናስራላህ ግድያ ባለፈው ሳምንት ይፈጸም እንጂ ለአመታት ያለመታከት መረጃ የማሰባሰብ፣ የመጥለፍ እና ሰላዮችን የማሰማራት ግዙፍ ዘመቻ ተካሂዷል።
በዚህ “አዲስ ስርአት” በሚል በተሰጠው ዘመቻ ላይ ሶስት የእስራኤል የስለላ ቡድኖች መሳተፋቸውን የዲዮዝ አሮኖዝ የተሰኘው የእስራኤል ጋዜጣ አስነብቧል።
እነዚህም “ዩኒት 8200”፣ “ዩኒት 9900” እና “ዩኒት 504” ናቸው።
እስራኤል 80 ቶን አሜሪካ ሰራሽ ቦምብ በማዝነብ የሄዝቦላሁን መሪ እንድትገድል ትልቁን ሚና የተጫወተው እንደ ሞሳድ ሁሉ ከሀገር ውጭ የሚካሄዱ ሚስጢራዊ ዘመቻውን የሚመራው “ዩኒት 504” ነው ይላል የየዲዮዝ አሮኖዝ ጋዜጣ ዘገባ።
ይሁን እንጂ የመጨረሻው እርምጃ በ“ዩኒት 504” እንዲፈጸም የሄዝቦላህ መሪዎችን መረጃ የሚመነትፈው “ዩኒት 8200” እና የመሪዎቹን እንቅስቃሴ የሚያሳዩ ምስሎችን በመመርመር መገኛ አቅጣጫቸውን የሚጠቁመው “ዩኒት 9900” ድርሻም የላቀ ነበር።
የእስራኤሉ የስለላ ድርጅት (ሞሳድ) የሄዝቦላህ መሪዎችን ለመግደል ሴራ መሸረብ ከጀመረ ረጅም አመታት መቆጠራቸውን ዘገባው ያክላል።
በተለይ የ2006ቱ የእስራኤልና ሄዝቦላህ ጦርነት ከተካሄደ በኋላ ዘመቻው መጠናከሩንም በማውሳት።
ስለ “ዩኒት 8200” እስካሁን የምናውቀው ምንድን ነው?
- የእስራኤል የስለላ ድርጅት (ሞሳድ) ዋነኛ ቅርንጫፍ ነው
- ወሳኝ መረጃዎችን፣ እቅዶችን እና የቢሆን ግምቶችን በመረጃ አስደግፎ ለጸጥታ ተቋማት ያቀርባል
- የጋዛ ነዋሪዎችን ስልክና ኮምፒውተሮችን በመጥለፍ መረጃዎችን እንደሚመነትፍ ይነገራል
- የፍልስጤማውያንን እንቅስቃሴ ለ24 ስአት ሳያቋርጥ እንዲከታተል ተልዕኮ ተሰጥቶታል
- በሃማስ ላይ የሚያደርገው ክትትል ደግሞ ከንጹሃን ፍልስጤማውያን በእጥፍ ያደገ ነው
“ዩኒት 9900”
የእስራኤል የብሮድካስት ባለስልጣን በሀምሌ ወር 2020 ባወጣው መረጃ መሰረት “ዩኒት 9900”፦
- የሚፈለጉ መሪዎችን ምስል ይሰበስባል፤ ያጠናል፤ የሚገኙበትን ትክክለኛ አቅጣጫ ከሳተላይት ምስሎች ጋር በማናበብ ይጠቁማል
- የአውደ ውጊያ ወሳኝ መረጃዎችን ያቀብላል
- የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከሳተላይት፣ ድሮኖች፣ ሴንሰሮች እና ከሰዎች የተገኙ መረጃዎችን አተናቅሮ ያቀርባል
- በውጊያ ወቅት የጠላት ሃይሎች የሚገኙባቸውን ስፍራዎች መረጃ ይሰጣል
- የስለላ መረጃዎቹን በጦር ሜዳ ለሚገኙ አዛዦች ይልካል
“ዩኒት 504”
- በእስራኤል የስለላ ዳይሬክቶሬት ስር ይገኛል
- ዋነኛ ስራው ከእስራኤል ውጭ የሚካሄዱ ልዩና ሚስጢራዊ ዘመቻዎችን ማካሄድ ነው
- የውጭ ሀገር ዜጎችን ለስለላ እየመለመለ ለተልዕኮ ዝግጁ ያደርጋል
- በ1948 ሲቋቋም “ሞዲን 10” የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ነበር፤ የመጀመሪያ መሪውም ዴቪድ ክሮን ይባላል
- በ1967ቱ የስድስት ቀናት ጦርነት እስረኞችን ከሚመለምለው ”ዩኒት 560” ጋር ተዋህዶ ነበር ፤ በ1973ቱ ጦርነት ስያሜውን በድጋሚ ወደ “ዩኒት 504” መልሷል
- በዴቪድ ክሮን እንደተመሰረተ ተጨማሪ አረብኛ ተናጋሪዎችን ቀጥሯል
የ”ዩኒት 504” ስኬታማ ተልዕኮዎች ውስጥ፦
- በመስከረም 1967 የቡድኑ ሰላዮች በካርቱም የተካሄደ ሚስጢራዊ ስብሰባ ይዘቶችን ማግኘት ችለዋል
- ከ1973ቱ ጦርነት (አራተኛው የእስራኤልና አረብ ሀገራት ጦርነት) በፊት የአረብ እና ከእስራኤል ጋር የሚዋሰኑ ሀገራትን ወታደራዊና ሌሎች ወሳኝ መረጃዎች አቅርቧል
- በ2019 የፍልስጤሙ ኢስላሚክ ጂሃድ መሪ ባሃ አቡ አልአታ ግድያ ላይ ተሳትፏል
የ”ዩኒት 504” ተሳትፎ በሊባኖስ
የእስራኤሉ ጋዜጣ “ጀሩሳሌም ፖስት” በህዳር ወር 2023 ባወጣው ዘገባ ሞሳድ በኢራን ላይ ትኩረቱን በማድረጉ “ዩኒት 504” በሊባኖስ የሚካሄዱ ዘመቻዎችን እንዲመራ መደረጉን ገልጾ ነበር።
ይህ የስለላ ቡድን ሙሉ ትኩረቱን በሊባኖስ ላይ በማድረጉም በጋዛ የሚካሄዱ የስለላ ስራዎችን ለእስራኤል የሀገር ውስጥ የደህንነት ተቋም “ሺን ቤት” መስጠቱንም ዘገባው ያክላል።
ሃማስ ባለፈው አመት በእስራኤል ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት እንደፈጸመ ግን “ዩኒት 540” በደቡባዊ እስራኤል ጊዜያዊ መቀመጫውን ገንብቶ ስራውን መጀመሩንም በመጥቀስ።
በሶሪያ የፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ተቃዋሚዎች ከእስራኤል ጋር ግጭት ውስጥ እንዳይገቡ በማሳመን ረገድ ትልቅ ድርሻ ነበረው የተባለው “ዩኒት 504” የውጭ ሀገር ዜጎችን ለስለላ የመመልመል ብቃቱ እስራኤል በተለያዩ ሀገራት ለፈጸመቻቸው ሚስጢራዊ ዘመቻዎች ትልቅ አበርክቶ ነበረው።
ስማቸው ያልተተቀሰ የቀድሞው የእስራኤል የደህንነት ባለስልጣን “በቅርቡ በተደረጉት ዘመቻዎች (የሃኒየህ ግድያ) ብዙ ሰዎች የሞሳድን የቴክኖሎጂ ምጥቀት ያነሳሉ፤ ይሁን እንጂ የሞሳድ ዋነኛው ሃይል በየሀገራቱ የመለመላቸው ሰላዮች ናቸው” ይላሉ።
በርግጥ በሊባኖስ በሄዝቦላህ አባላት እጅ የነበሩ የሬዲዮ መገናኛ መሳሪያዎች እና “ፔጀር” የተሰኙ መልዕክት መለዋወጫዎች እንዲፈነዱ በማድረግ የቡድኑን የግንኙነት መስመር ለመበጠስ የተካሄደው ዘመቻም የሞሳድን የቴክኖሎጂ አቅም እንዳሳየ በርካቶች ይስማሙበታል፤ ምንም እንኳን የስለላ ድርጅቱ ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ እጁ እንዳለበት እስካሁን በይፋ ባይገልጽም።