ዘላቂ ልማታቸው አርአያ የሚሆን ሶስት የአለማችን ከተሞች
የአርተንቲናዋ ሮዛሪዮ፣ የሜክሶኮዋ ጓዳላራጃ እና የታይላንዷ ባንኮክ ከባቢ አየርን በሚጠብቅ ልማታቸው ይወደሳሉ
የከተሞቹ የሃይል አጠቃቀምና የአረንጓዴ ልማት ለአለማችን ከተሞች በአርአያነት ሊወሰድ የሚችል ነው ተብሏል
የከተሞች ፈጣን ልማት የመንግስታቱ ድርጅት በ2050 አሳካዋለው ካለው የአየር ብክለትን ዜሮ የማድረስ ግብ አንጻር ተስተካክሎ መሄድ እንዳልቻለ ይነገራል።
የከተሞች እድገት የሚያመጧቸው ግዙፍ ፍላጎቶች እና ይህን ተከትሎም የሚከሰተው የከባቢ አየር ብክለት እየጨመረ መምጣቱንም ጥናቶች ያሳያሉ።
ከተሞች ከአለማችን የቆዳ ስፋት 3 በመቶውን ብቻ ቢሸፍኑም የሃይል ፍጆታቸው እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ የከባቢ አየርን በመበከል ረገድ ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ።
ቀጥሎ የተዘረዘሩት ሶስት ከተሞች ግን እድገታቸውን ከአየር ንብረት ጥበቃ ጋር ያወዳጁ፣ የሚያስከትለውን ጉዳትም አስቀድመው ለመከላከል የሚሰሩ ናቸው።
ወርልድ ሪሶርስ ኢንስቲትዩትም ከተሞቹ ለሌሎች የአለማችን ከተሞች አርአያ ይሆናሉ ብሏቸዋል።
1. ሮዛሪዮ - አርጀንቲና
በፈረንጆቹ 2007 ከባድ የጎርፍ አደጋ የገጠማት ሮዛሪዮ በጎርፍ አደጋ ተጠቂ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት እና ወደ ልማት ስፍራነት በመቀየር የምግብ ዋስትና ችግሯን ቀርፋለች።
ከተማዋ ጎርፍ የሚያጠቃቸው ስፍራዎች ላይ አትክልትና የተለያዩ ሰብሎችን በመዝራት በጎርፍ ይጥለቀለቁ የነበሩና ቆሻሻ የሚጣልባቸውን አካባቢዎች ጽዱና አረንጓዴ አድርጋለች።
ሮዛሪዮ የከተማ ግብርናን በ10 አመት የልማት እቅዷ ውስጥ በማከተትም የከተማዋን ጽዳት ከመለወጥ ባሻገር የበርካቶችን የምግብ ዋስትና ጥያቄ መፍታት ከጀመረች ሰነባብታለች ተብሏል።
2. ጓዳላራጃ - ሜክሲኮ
የሜክሲኮዋ ጓዳላራጃ ደግሞ ከባቢ አየርን የማይበክል ትራንስፖርትን በማበረታታት ፈር ቀዳጅ መሆኗ ተነግሮላታል።
ከተማዋ ከፈረንጆቹ 2003 ጀምሮ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ዋና ዋና መንገዶቿን ትዘጋለች። በመንገዶቹ መንቀሳቀስ የሚቻለውም በሳይክሎች ብቻ ነው።
በኮሎምቢያ ቦጎታም መሰል እንቅስቃሴ ቢደረግም እንደ ሜክሲኮዋ ጓዳላራጃ ባህል አልሆነም።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም ንቅናቄውን ደግፈውት በ2010 በከተማዋ ለሞተር ተሽከርካሪዎች የሚውሉ አውራ መንገዶች እንዳይገነቡ የሚጠይቅ ህግ እንዲወጣ እስከማድረስ ችለዋል።
የጓዳላራጃ ማስተር ፕላንም ከአየር ብክለት ነጻ ለሆኑና ጤናማ የትራንስፖርት አማራጮት ትኩረት በሚሰጥ መልኩ ተዘጋጅቷል ነው የተባለው።
3. ታይላንድ - ባንኮክ
የንግድ ማዕከሏ ታይላንድም ዘላቂና ፈጣን ልማቷ በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ያሉ ሰዎችን ያልገፋ መሆኑ ተገልጿል።
ከተማዋ ከ2003 ጀምሮ በጎርፍ ተጠቂ የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ቤቶች ዳግም ገንብታለች።
ግንባታውም ሰዎቹን ከጎርፍ አደጋ ከመጠበቁ ባሻገር የቀደመ ህይወታቸውን በማይረብሽ መልኩ መካሄዱን የሚጠቅሰው ወርልድ ሪሶርስ ኢንስቲትዩት፥ በዚህም ማህበረሰቡን የመፍትሄው አካል ማድረጓን ያነሳል።
በረጃጅም ህንጻዎቿ የምትታወቀው ባንኮክ ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ ነዋሪዎቿን ያለመዘንጋቷና የወሰደችው እርምጃ ተወድሷል።
ባንኮክም ሆነች ሮዛሪዮ የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን ለመቀነስ እያከናወኗቸው ካሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ሌሎች የአለማችን ከተሞች ተሞክሮ ሊወስዱኡ ይገባል ተብሏል።