አየርላንድ የአየር ብክለትን ለመከላከል 200 ሺህ ላሞችን ልታርድ ነው
ሀገሪቱ ወደ ከባቢ አየር የሚላኩ በካይ ጋዞችን የመቀነስ የረጅም ጊዜ እቅድ አላት
የግብርና ዘርፍ ወደ ከባቢ አየር ከሚለቀቀው በካይ ጋዝ ውስጥ የ33 በመቶ ድርሻ አለው ተብሏል
አየርላንድ የአየር ብክለትን ለመከላከል 200 ሺህ ላሞችን ልትቀንስ ነው፡፡
በወተት ምርቷ የምትታወቀው አየርላንድ ከላሞቿ የሚለቀቀውን በካይ ጋዝ ለመቀነስ እምጃ መውሰድ መጀመሯን አስታውቃለች፡፡
አየር ላንድ በፈረንጆቹ 2030 ላይ ከግብርና መስክ ወደ ከባቢአየር የሚለቀቀውን የበካይ ጋዝ መጠን በ30 በመቶ የመቀነስ እቅድ አውጥታለች፡፡
በዚህ መሰረትም በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ውስጥ ብቻ 200 ሺህ ላሞችን እንደምታስወግድ ሀገሪቱ ግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የሀገሪቱ ላም አርቢዎች ማህበር እንዳለው በገበሬዎች እና በአየርላንድ መንግስት መካከል ውይይት በመካሄድ ላይ መሆኑን ገልጿል፡፡
ማህበሩ በበኩሉ የወተት ላሞችን የማስወገዱ ስራ በበጎ ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባል ሲል ቢያሳስብም የሀገሪቱ ግብርና ሚኒስቴር ግን ለእቅዱ የድጎማ በጀት ማመቻቸቱን አስታውቋል፡፡
አየርላንድ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ያወጣችውን እቅድ ለመተግበር ትግል ላይ መሆኗን የገለጸች ሲሆን ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀው በካይ ጋዝ መጠን ከዚህ በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር የ30 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል ተብሏል፡፡
የዓለም ግብርና ዘርፍ ለዓለማችን በካይ ጋዝ የ33 በመቶ ድርሻ አለው የተባለ ሲሆን አሜሪካንን ጨምሮ ሰፋፊ የግብርና ስራዎችን የሚከተሉ ተቋማት ለበካይ ጋዝ ልቀት ትኩረት እንዲሰጡ ተጠይቀዋል፡፡
እንደ ቢልጌት ያሉ ባለጸጋዎችም ግብርና በታዳሽ ሀይል አማራጮች ላይ እንዲመሰረት ድጋፉ እንዲያደርጉም ጥሪ ቀርቦላቸዋል ተብሏል፡፡