አሜሪካ ከአለም ባንክ እና አይኤምኤፍ አባልነት ብትወጣ ምን ሊፈጠር ይችላል?
ለሁለቱም አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ከፍተኛ ድጋፍ የምታደርገው አሜሪካ ለአይኤምኤፍ ብቻ በአመት ከ117 ቢሊየን ዶላር በላይ ትሰጣለች

የትራምፕ አስተዳደር በቅርቡ ከገንዘብ ተቋማቱ አባልነት ለመውጣት እያጤነ እንደሚገኝ መረጃዎች እየወጡ ነው
ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ማብቃት በኋላ በምዕራባውያን የተመሰረቱት የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና የአለም ባንክ በአለም አቀፍ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እና የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳላቸው ይነገራል፡፡
በዘንድሮው የቡድን 20 አባል ሀገራት የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ያልተሳተፈችው አሜሪካ ከገንዘብ ተቋማቱ አባልነት ልትወጣ እንደምትችል እየተነገረ ነው፡፡
ይህ ውሳኔ የሚያስከትለው ተጽዕኖን ለመረዳት የተቋማቱን ሚና እና አመሰራረት እንመልከት፦
የሁለቱ የገንዘብ ተቋማት አለም አቀፋዊ ሚና ምንድን ነው?
ከገንዘብ እንቅስቃሴ እና የበጀት ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰራው አይኤምኤፍ የክፍያ ሚዛን ቀውሶችን ለማስተካከከል፣ የሀገራት የበጀት ጉድለት እና የብድር ምጣኔዎችን ማሻሻል ላይ ይሰራል፡፡
ተቋሙ ብድሮችን ከመልቀቁ በፊት የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ይታወቃል፡፡
ከእነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች መካከል የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያዎች፣ የሚባክኑ የመንግስት ወጪዎችን መቀነስ፣ ነጻ እና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚን ማስተዋወቅ፣ የመንግስት ድጎማን ማስቀረት፣ ሙስና እና ብልሹ አሰራርን መቀነስ፣ ግልጽ የሆነ የበጀት አስተዳደር፣ የታክስ ገቢን ማሳደግ እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡
ክፍያዎችን ከኢኮኖሚ አፈጻጸም ጋር የሚያገናኙ አበዳሪዎች ለተበዳሪዎች የሚሰጡትን ብድር ለመወሰን የአይኤምኤፍ መረጃን እንደመለኪያ ይጠቀማሉ፡፡
ከባቡር ሀዲድ እስከ ጎርፍ እርከን ድረስ የልማት እና የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ የሚያተኩረው ደግሞ የአለም ባንክ ነው፡፡
ባንኩ በዋናነት በትምህርት፣ ጤና፣ መንገድ፣ የመጠጥ ውሀ፣ እርሻ፣ ኢነርጂ እና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች ላይ ለሀገራት በአነስተኛ ወለድ ገንዘብ ይሰጣል፡፡
የአይኤምኤፍ ድጋፍ የሚስፈልጋቸው እነማን ናቸው?
በአሁኑ ወቅት ተቋሙ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለ90 ሀገራት ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን አርጄንቲና ያለ ተቋሙ ድጋፍ ለመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ መክፈል አትችልም፡፡
ሴኔጋል እና ሲሪላንካን የመሳሰሉ ሀገራት የጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴያቸው በአይኤምኤፍ ድጋፍ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
የመንግስታት ከአይኤምኤፍ ጋር መስራት ለግል እና ለባለብዙ ወገን ባለሀብቶች ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ማስተማመኛ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡
በተመሳሳይ በግል እና በመንግስት ትብብር በሚሰሩ ፕሮጀክቶች ላይ የአለም ባንክ ድጋፍ መኖርን ባለሀብቶች ለዋስትና ይፈልጉታል፡፡
አሜሪካን ጨምሮ ለአለም ባንክ እና አይኤምኤፍ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ ያደጉ ሀገራት የገንዘብ ተቋማቱን ከብድር ያለፈ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ የበላይነትን ለማረጋገጥ እንደሚጠቀሙባቸው ቢነገርም ዓለም አቀፍ የፋይናንስ መረጋጋትን ለማረጋገጥ እና መንግስታት የበጀት ወጪያቸውን በራሳቸው መሸፈን እንዲችሉ እገዛ ያደርጉባቸዋል፡፡
አሜሪካ ከእነዚህ አለም አቀፋዊ የገንዘብ ተቋማት ብትወጣ ምን ሊፈጠር ይችላል?
ለውጭ ሀገራት የሚደረጉ የድጋፍ ወጪዎችን በመቀነስ በአሜሪካ ውስጥ ለማዋል እቅድ እንዳላቸው የሚገልጹት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ዋሽንግተንን በቢሊየን ዶላር ገንዘብ ወጪ ከምታደርግባቸው አለም አቀፋዊ እና ቀጠናዊ ድርጅቶች ለማስወጣት እቅድ ይዘዋል፡፡
እስካሁን የአሜሪካ አለማቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) ድጋፍ መቋረጥ እና ከአለም ጤና ድርጅት አባልነት መውጣት በዋናነት የሚጠቀሱ ሲሆን፥ በቀጣይ ከመንግስታቱ ድርጅት፣ ከኔቶ አሁን ደግሞ ከአይኤምኤፍ እና ከአለም ባንክ አባልነት ለመውጣት እየዛቱ ነው፡፡
ሀገሪቱ በአመት ለአይኤምኤፍ ከ117 ቢሊየን ዶላር በላይ፤ ለአለም ባንክ ደግሞ 59 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ የምታደርግ ሲሆን ይህም በሁለቱም ተቋማት 16 በመቶ መዋጮን የምትሸፍነው ሀገር ያደርጋታል፡፡
ይህን ተከትሎም አሜሪካ ከድርጅቱ አባልነት የምትወጣ ከሆነ በአለም አቀፍ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጠባሳ ሊያሳርፍ እንደሚችል የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡
የብድር አስተዳደር እና የገንዘብ ገበያ ባለሙያው ካን ናዚል “ይህ ውሳኔ ተግባራዊ ከሆነ የአለም ኢኮኖሚን ሊያንኮታኩት የሚችል ነው” ብለዋል፡፡
በተለይ በሁለቱ የገንዘብ ተቋማት በጀታቸውን የሚያንቀሳቅሱ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ታዳጊ ሀገራት ኢኮኖሚ በብዙ እጥፍ ወደ ኋላ ሊመለስ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ባለሙያው አክለውም አሜሪካ በአይኤምኤፍ ባላት ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ የተነሳ የአለም ኢኮኖሚን መዘወር የምትችልበት ሀይል እንደተጎናጸፈች ያነሳሉ፡፡
በዚህም አሜሪካ ከአባልነት በመውጣት የምትፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ቻይና ቀዳሚዋ ሀገር እንደምትሆን ይህ ደግሞ የዋሽንግተንን አቅም ወደ ቤጂንግ እንደሚያዞር ጠቅሰዋል፡፡
ቻይና በአሁኑ ወቅት በአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ ያላት የአክሲዮን ድርሻ አምስት በመቶ ብቻ ነው፡፡