ዩክሬን ለመልሶ ግንባታ ከግማሽ ትሪሊየን ዶላር በላይ ያስፈልጋታል - የአለም ባንክ
በጦርነቱ የደረሰው ውድመት ከባለፈው አመት ከተሰራው ግምገማ አንጻር በ7 በመቶ ጨምሯል

የመኖሪያ ቤቶች፣ የትራንስፖርት እና የሀይል መሰረተ ልማቶች በጦርነቱ ክፉኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል
ዩክሬንን መልሶ ለመገንባት በ2024 የተገመተው ወጪ በሶስት ዕጥፍ መጨመሩን የአለም ባንክ አስታወቀ፡፡
የፈረሱ መሰረተ ልማቶችን እና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ዳግም ለመገንባት የሚያስፈልገው ገንዘብ 524 ቢሊየን ዶላር እንደሚጠጋ ባንኩ ባወጣው ሪፖርት አመላክቷል፡፡
በተቋሙ አዲስ ይፋ የተደረገው የጥናት ውጤት የሶስት አመት የጦርነቱን ጊዜ የሚያጠቃልል ሲሆን በዩክሬን የኃይል መሠረተ ልማት ላይ የደረሰው ጉዳት 70 በመቶ መጨመሩን ጠቅሷል፡፡
የጉዳት መጠኑ ከአንድ አመት በፊት ከነበረው 486 ቢሊዮን ዶላር የመጨረሻ ግምት ከ7 በመቶ በላይ ብልጫ አሳይቷል፡፡
የመኖሪያ ቤት፣ ትራንስፖርት፣ ኢነርጂ፣ ንግድ እና ትምህርት ክፉኛ ጉዳት የደረሰባቸው ዘርፎች ሲሆኑ በመኖሪያ ቤቶች የደረሰው ጉዳት ከ2.5 ሚሊየን በላይ ቤተሰቦችን እንደሚጎዳ ነው የተነገረው
ጥናቱ በህንፃዎች እና በሌሎች የመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ የሚደርሰውን ቀጥተኛ አካላዊ ጉዳት፣ በሰዎች ህይወት እና ኑሮ ላይ የሚኖረውን ተፅእኖ እና በተሻለ ሁኔታ ለመገንባት ያለውን ወጪ በመለካት ማካተቱን ገልጿል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያ እና ዩክሬን ጋር በተናጥል ጦርነቱ እንዲቆም ግፊት እያደረጉ ሲሆን፤ ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ባደረጉት ውይይት በሳምንታት ውስጥ ስምምነት ላይ ሊደረስ እንደሚችል ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የዩክሬን ጠቅላይ ሚኒስትር ዴኒስ ሽሚሃል በሰጡት መግለጫ ባለፈው አንድ ዓመት የዩክሬን የማገገሚያ ወጪ እያደገ የቀጠለው ሩሲያ እየደረሰች የምትገኘው ጥቃት በመጠናከሩ ነው ብለዋል፡፡
የዩክሬን መንግስት ለ2025 ቅድሚያ ለሚሰጣቸው የመንግስት ወጪዎች እና አገልግሎቶች ከአጋር አካላት ባገኘው ድጋፍ 7 ቢሊየን ዶላር መድቦ የነበረ ቢሆንም አሁንም ወደ 10 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የፋይናንስ ክፍተት እንዳለበት የአለም ባንክ መግለጫ ገልጿል።
አሁናዊው የባንኩ የጉዳት ግምገማ ሩስያ በዩክሬን ላይ በምትፈጽማቸው ጥቃቶች የሚደርሱ ቀጥተኛ ጉዳቶች በየካቲት 2024 ከተገለጸው 152 ቢሊዮን ዶላር ወደ 176 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ማለቱን ያሳያል፡፡
በሃይል ዘርፍ የተበላሹ ወይም የወደሙ ንብረቶች በ 70 በመቶ ጨምሯል፤ የኃይል ማመንጫ፣ ማስተላለፊያ፣ ማከፋፈያ እና የዲስትሪክት መሰረተ ልማቶች ተጎድተዋል ተብሏል፡፡
በመኖሪያ ቤት 84 ቢሊዮን ዶላር ፣ በትራንስፖርት 78 ቢሊዮን ዶላር ፣ በኢነርጂ እና ማዕድን 68 ቢሊዮን ዶላር ፣ በንግድ እና ኢንዱስትሪ ከ64 ቢሊዮን ዶላር በላይ እና በግብርና ከ55 ቢሊዮን ዶላር በላይ ጉዳት መመዝገቡንም ነው የአለም ባንክ ያስታወቀው፡፡