በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ቀጣና ያሉ ነዋሪዎች ሰቆቃ
በክልሉ የመንግስት ተቋማት አመራሮች እና ነጋዴዎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ከታሰሩ አንድ ወር አልፏቸዋል ተብሏል
18 ወራት ባስቆጠረው ጦርነት ንጹሃን በእገታ፣ ዘረፋ እና ሌሎች የሰብዓዊ ቀውስ መዳረጋቸውን ተናግረዋል
በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ቀጣና ያሉ ነዋሪዎች ሰቆቃ
የፌደራል መንግስት ክልል የክልል ልዩ ሀይሎችን ዳግም አደራጃለሁ በሚል ውሳኔ ካሳለፈበት ሚያዝያ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች አማካኝነት ጦርነት ተቀስቅሷል፡፡
በክልሉ ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ አዋጅ ከ10 ወራት በኋላ ያልተራዘመ ቢሆንም አሁንም በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ጦርነቶች እየተካሄዱ ናቸው፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና እና የክልሉ ኮሙንኬሽን ከፍተኛ አመራሮች በክልሉ “ህግ የማስከበር እርምጃው” ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡
ይህን ተከትሎ አል ዐይን አማርኛ በክልሉ ዋና ዋና ከተሞች እና ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች እየተካሄዱ ባሉ ከባድ ውጊያዎች ንጹሃን ምን ያህል ከጥቃት ተጠብቀዋል ሲል ነዋሪዎችን አነጋግሯል፡፡
ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የላሊበላ ከተማ ነዋሪ እንዳሉን ከተማውን ጨምሮ በዙሪያው ባሉ ቦታዎች እየተካሄደ ያለው ነገር የቀድሞውን አስተዳድር የሚስናፍቅ ነው ብለዋል፡፡
“ሰው በሰላም አድሮ በሰላም መገናኘት ብርቅ የሆነበት ወቅት ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱ አያንቀሳቅስም፡፡ ህዝቡ ስነ ልቦናው ላሽቋል፣ ጭንቅት እና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ነው፡፡ መቼ ነው ደህና ቀን የሚመጣው እያልን ጭንቀት ላይ ነን፡፡ ፋኖም ሆነ መከላከያ እየተዋጉ ያሉት አላማ ይዘን ነው ቢሉም ለህዝብ አለማሰባቸው ያሳዝናል“ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በርካታ የከተማው ነዋሪ እየታሰሩ እና ወደ ሌሎች ከተሞች በአውቶቡስ እየተወሰዱ ነው የሚሉት እኝህ አስተያየት ሰጪ በየጊዜው ውጊያ በመቀስቀሱ ምክንያት ህጻናት የተኩስ ድምጽ ሲሰሙ ያለቅሳሉ፣ ይጨነቃሉ ፣መተኛትም አልቻሉም ብለዋል፡፡
ላሊበላ ከተማ ውስጥ ያሉ ትምህርት ቤቶች የተወሰኑ ተማሪዎችን ተቀብለው እያስተማሩ ቢሆንም ከከተማ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያሉ ትምህርት ቤቶች ግን እንደተዘጉ መሆናቸውንም አስተያየት ሰጪው ነግረውናል፡፡
“አንድ ማህበረሰብ አልተከበርኩም፣ በማንነቴ እየተገደልኩ ነው በሚል ትጥቅ አንስቶ ወደ ውጊያ የገባን አካል ማቃለል እና ጥያቄውን ማሳነስ ተገቢ አይደለም” ያሉት አስተያየት ሰጪው “የአንድ ቤተሰብ አባላት አንዱ ልዩ ሀይል እንዱ ፋኖ ሌላኛው የሀገር መከላከያ አባል ሆኖ ነው እየተዋጋ ያለው፡፡ እሚሻለው የህዝብን ጥያቄ በወጉ ማድመጥ እና ምን ይሻላል ማለቱ ነበር፡፡ መንግስት ብዙ ሀላፊነት ነበረበት የጎረምሳ ስራ ነው እየሰራ ያለው” ሲሉም አክለዋል፡፡
አስተያየት ሰጪው አክለውም ላሊበላ ከተማ በጎብኚዎች ስትጨናነቅ የነበረች እና በቀን እስከ ሶስት ጊዜ እና በላይ በረራ ይደረግባት የነበረች ከተማ አሁን ላይ በጦርነቱ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ ጎብኚዎች መምጣት ካለመቻላቸው ባለፈ ባለሆቴሎች እየለቀቁ ወደ ሌሎች ከተሞች እየተሰደዱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል ከተሞች ሰዎች በገፍ እየታሰሩ መሆኑ ተገለጸ
ስራ መጥፋቱ፣ እስር እና ድብደባ የተለመደ ቢሆንም ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች የሚፈጸመው እገታ አሳሳቢ ሆኗል ያሉን ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪው የባህርዳር ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡
በቀበሌ አራት እንደሚኖሩ እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ እኝህ የከተማዋ ነዋሪ እንዳሉን “እገታን በመፍራት አቅም ያላቸው ሰዎች ወደ አዲስ አበባ እየተሰደዱ ነው፣ አጋቾች በአንድ ሰው እስከ 6 ሚሊዮን ብር እንዲከፈላቸው እየጠየቁ ነው” ብለዋል፡፡
”ስራ ካቆምኩ አንድ ዓመት አለፈኝ” የሚሉት አስተያየት ሰጪው “ቤተሰቤን ለመመገብ የማደርገው ጠፍቶኛል፣ የኑሮ ውድነቱ ሊገድለን ነው፡፡ ለምን ሰላም እንደማይሰፍን ሳስብ ነገሩ ያበሳጫል” ብለዋል፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ በምስራቅ ጎጃም ዞን ስር ካሉ ወረዳዎች አንዷ በሆነችው እናርጅ እናውጋ ወረዳ በደብረ ወርቅ ከተማ ይኖራሉ፡፡
እንደ አስተያየት ሰጪው ከሆነ ከሰሞኑ ፈለገ ብርሃን፣ገደብ እና ዲማ በተሰኙ ቦታዎች ላይ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ፋኖ መካከል በተደረጉ ከባድ ውጊያዎች አርሶ አደሮችን ጨምሮ ንጹሃን እንደተገደሉ ነግረውናል፡፡
ከሶስት ቀናት በፊትም ንዋየ ማርያም በተባለ ቦታ ለይ በነበረ አንድ ትምህርት ቤት ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ትምህርት ቤቱ ወድሞ ማየታቸውን እኘህ አስተያየት ሰጪ ተናግረዋል፡፡
በወረዳው ዋና ከተማ ደብረወርቅ ካሉ የመንግስት ተቋማት መካከል ከጤና ውጭ ያሉ ተቋማት ስራ እየሰሩ እንዳልሆነ የተናገሩት አስተያየት ሰጪው አልፎ አልፎ የፖለቲካ አመራሮች ቢሮ እንደሚገቡ እና እነሱ ወደ ቢሮ በገቡበት ወቅት ከስራ የቀረ የመንግስት ሰራተኛ የወር ደመወዙን እንደሚያጣም አክለዋል፡፡
ባለፉት አራት ሳምንታት ውስጥ ሰዎች በገፍ እየታሰሩ ነው፣ ነጋዴዎች እና የሆቴል ባለቤቶች ዋናው የእስሩ ሰላባ ሆነዋል የሚሉት እኝህ አስተያየት ሰጪ የታሰሩት ሰዎች ወደ ዳንጋላ ከተማ እንደተወሰዱም ነግረውናል፡፡
“የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች የጦር መሳሪያ የተመዘገበውንም ሆነ ያልተመዘገበውን በገፍ ከህዝቡ እያስወረዱ ነው” የሚሉት አስተያየት ሰጪው “ማንኛውም ሰው መሳሪያህን አምጣ ተብሎ ካልሰጠ ለክላሽ 175 ሺህ ለቃታ መሳሪያ ደግሞ 90 ሺህ ብር ያስከፍላሉ፡፡ ተገደህ ለምትከፍለው ገንዘብ ደረሰኝ ከጠየቅህ ደግሞ ድብደባው እና እስሩ በዛው ልክ ይከፋል፣ ቂም ያለበት ሰው ከጠቆመብህ ትያዛለህ አለው የተባልከውን መሳሪያ ዋጋ ክፈል ይሉሃል” ሲልም ነግሮናል፡፡
አስተያየት ሰጪው አክለውም “በህይወት መኖር ከባድ ሆኗል፡፡ የአብዛኛው ሰው ፍላጎት ይህ ነው ሌላው ቅንጦት ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ቀንም ሌሊትም ቤት ውስጥ ነው፡፡ ከዛሬ ነገ የሆነ ሰው ጠቆመብን፣ በተባራሪ ጥይት ተመታን፣ ታፈስን ብለን በሰቆቃ ነው የምንኖረው” ብለዋል፡፡
ከመስቀል በዓል በኋላ ጀምሮ የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ንግዳቸውን በሰላም ሲሰሩ የነበሩ እና የቀን ሰራተኞችን ሳይቀር ፋኖን ትረዳላችሁ እያሉ በጅምላ እያሰሩ ነው ያሉን ደግሞ ሌላኛው የሸዋሮቢት ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡
እስሩ ከነዋሪዎች ባለፈም የመንግስት ተሿሚዎችንም ያካተተ እንደሆነ የሚናገሩት አስተያየት ሰጪው የታሰሩ ሰዎች በሰሜን ሸዋ እና አጎራባች ከሆኑ ዞኖች ስር ካሉ ወረዳዎች እና ከተሞች ወደ ሸዋሮቢት በማምጣት መታሰራቸውንም ከነዋሪው ሰምተናል፡፡
የክልሉ መንግስት ከነዋሪዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ያለውን ምላሽ ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከሰሞኑ ባወጣቸው ተከታታይ ሪፖርቶች በአማራ ክልል ንጹሃን ከጥቃት እየተጠበቁ እንዳልሆነ እና ምሁራንን ጨምሮ ሰዎች በጅምላ እየታሰሩ እንደሆነ ገልጿል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ ያሉ የሙያ ማህበራት በጸጥታ ችግሮች ምክንያት ስራቸው ከመስተጓጎሉ ባለፈ የባለሙያዎች እስር እና ሌሎች ጉዳቶች እየደረሱባቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የአማራ ክልል ዳኞች ማህበር ለአል-ዐይን እንዳለው በክልሉ ያለው የደህንነት ችግር ዳኞች በነጻነት ስራቸውን እንዳይሰሩ እክል መፍጠሩን ገልጾ ባለፉት ቀናት ውስጥም 13 ዳኞች ታስረውብኛል ብሏል፡፡
ከታሰሩት ውስጥ አራት ዳኞች ከእስር መለቀቃቸውን የተናገረው ማህበሩ ቀሪ እና በእስር ላይ ያሉ ዳኞች እንዲለቀቁም ጥሪ አቅርቧል፡፡
የአማራ ክልል ጤና ባለሙያዎች ማህበር በበኩሉ የጤና ባለሙያዎች በክልሉ በቀጠለው ጦርነት ምክንያት ለግድያ፣ እስር እና ለተለያዩ እንግልቶች መዳረጋቸውን አስታውቋል፡፡