በሱዳን በጎርፍ አደጋ ህይወታቸው ያለፈ ዜጎች ቁጥር ወደ 89 አሻቀበ
አለም አቀፉ የቀውስ አስተዳድር ቡድን እና ህጻናት አድን ድርጅት ለሱዳናዊያን የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ ጠይቀዋል
ከሰኔ ወር አንስቶ በጎርፍ ምክንያት 146 ሺህ ዜጎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል
በሱዳን በጎርፍ አደጋ ህይወታቸው ያለፈ ዜጎች ቁጥር ወደ 89 ማሻቀቡ ተነግሯል።
ጎረቤት ሀገር ሱዳን በከባድ ዝናብና ጎርፍ መቸገሯ ተገልጿል።
ካሳለፍነው ሰኔ ወር ጀምሮ ባሉት ሶስት ወራት ውስጥ በጎርፍ የተወሰዱ ዜጎች ቁጥር 89 መድረሱን ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል።
በሱዳን በዚህ ሳምንት ብቻ 77 ሰዎች በጎርፍ ተወስደዋል
ባሳለፍነው ሳምንት ብቻ ብሉ ናይል ተብሎ በሚጠራው የሃገሪቱ አካባቢ ብቻ 77 ሱዳናውያን በጎርፍ ተወስደዋል ተብሏል።
አሁን በወጣ መረጃ ደግሞ የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋው የጨመረ ሲሆን 44 ሺህ መኖሪያ ቤቶች በጎርፍ መወሰዳቸው ተገልጿል።
የጎርፍ አደጋው በተለይም በመስከረም ወር ላይ እንደሚጨምር የተገለጸ ሲሆን ተጨማሪ ዜጎች ሊሞቱ እና ንብረቶች ሊወድሙ እንደሚችሉ ዓለም አቀፉ የቀውስ አስተዳድር ወይም ክራይስስ ግሩፕ አስጠንቅቋል።
አለም አቀፉ የቀውስ አስተዳድር ቡድን እና ህጻናት አድን ድርጅት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ተቋማት ለሱዳናዊያን የገንዘብ ድጋፍ እንዲደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር መንግስት በስድስት የሀገሪቱ ግዛቶች የአስቸኳይ ጊዜ ያወጀ ሲሆን፤ የረድዔት ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉለትም ጥሪ አቅርቧል።
በአደጋው እስካሁን ከ44 ሺህ በላይ ቤቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውና ከ146 ሺህ በላይ ሱዳናዊያን ደግሞ ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለዋል።
እንደ ዘገባው ከሆነ በአደጋው ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ሌሎች የህዝብ መገልገያ መሠረተ ልማቶችም ወድመዋል።
የአደጋው ሰለባዎችም መኖሪያቸውን አጥተው በጊዜያዊነት በድንኳን ውስጥ ለመጠለል እና እርዳታ ለመጠባበቅ ተገደዋል ተብሏል።
ከአንዳንድ በጎ ፈቃደኞች እና የአካባቢው የበጎ አድራጎት ተቋማት ከሚያገኙት ድጋፍ በስተቀር የሃገራቸው መንግስት እየደገፋቸው እንዳይደለም ነው የገለፁት።