በአፍሪካ የአየር ንብረት ለዉጥ ጉዳት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መሆኑ ተገለጸ
ባለፉት 20 ዓመታት የአየር ንብረት ለዉጥ የአፍሪካን አጠቃላይ ኢኮኖምያዊና ማህበራዊ ልማት በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳ መሆኑን የአፍሪካ ህብረት ገለጸ፡፡
በነነዚህ ዓመታት ውስጥ የአየር ንብረት መዛባት ችግር በአፍሪካ እየጨመረ ሲሆን ከወራት በፊት የተከሰተው ‘ሳይክሎን አይዳይ’ በተሰኘዉ አዉሎ ንፋስ ብቻ በማላዊ፣ሞዛምቢክና ዚምባብዌ ከ 1 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸው ችግሩ እየጨመረ ለመሆኑ ማሳያ እንደሆነ ሲጂቲን አፍሪካ ዘግቧል፡፡
በሞዛምቢክና በኮሞሮስ በድጋሚ ባጋጠመው በአውሎ ንፋስ የመመታት አደጋ ወደ 2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚደርስ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ መድረሱን የፓን አፍሪካ ቡድን አስረድቷል፡፡
በቅርቡ የዓለም ባንክ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመለክተው ባለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት ውስጥ በርካታ የአፍሪካ አገራት 4.5 በመቶ አመታዊ እድገት ቢያሳዩም የውሃ ና የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች ስጋት መደቀናቸው ተገልጿል፡፡
በመሆኑም ህብረቱ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ተኮር አጀንዳዎች፣ የፓሪስ ስምምነት፣ ዘላቂ የልማት ግቦችና አዲሱን የከተማ አጀንዳ የመተግበር አስፈላጊነት ላይ ትኩረት ማድረጉ ተጠቅሷል፡፡
የአየር ሁኔታን በተመለከተ የተዘጋጁት ፖሊሲና ስትራተጂዎች በተግባር ወደ ስራ እንዲገቡ በማድረግ ለውጥ መታየት አለበት የተባለ ሲሆን፣ ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ሀብት በማሰባሰብ የተያዙ ግቦችን ለማሳካት ጥረት ማድረግ እንዳለባቸውም ተገልጿል።
ምንጭ፡- ሲጂቲኤን