በአለም ሙቀት መጨመር በ2021 470 ቢሊየን የስራ ስአት ባክኗል - ጥናት
ላንሴት ያደረገው ጥናት በ2030 ከጠቅላላው የስራ ስአት 2 ነጥብ 2 በመቶው በሙቀት መጨመር ምክንያት እንደሚባክን አሳይቷል
በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚባክነው የስራ ስአት የ80 ሚሊየን ሰዎች የሙሉ ጊዜ ስራን ይሸፍናል
የአለም የአየር ንብረት ለውጥ በሰራተኞች ጤና እና በስራ ስአት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሰ መሆኑን አንድ ጥናት አመላከተ።
የአለም የሰራተኞች ድርጅት ሰራተኞች ከ35 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ የሆነ ሙቀት እና ወበቅን መቋቋም እንደማይችሉና ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳድርባቸው ይገልጻል።
በላንሴት ሜዲካል ጆርናል ላይ የወጣ ጥናትም እየጨመረ የመጣው የአለም ሙቀት በሰራተኞች ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ በዝርዝር አመላክቷል።
የአለም ሙቀት መጨመር በ2021 ብቻ 470 ቢሊየን የስራ ስአት መባከኑን ያመላከተው ጥናቱ፥ በተለይ አነስተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት ተጎጂ መሆናቸውን ጠቅሷል።
- በአየር ንብረት ለውጥ ድርድር የሌለው የሙቀት መጨመርን መቀነስ ነው- ዶ/ር ሱልጣን አል ጃብር
- ታይላንድ በከፍተኛ ሙቀት ሳቢያ ነዋሪዎቿ ከቤት እንዳይወጡ አስጠነቀቀች
ከአል ዐይን ኒውስ ጋር ቆይታ ያደረጉት በአለም ሰራተኞች ድርጅት የጥናት ክፍል ዳይሬክተሩ ኒኮላስ ማይተር የአለም ሙቀት መጨመር በሰራተኞች ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ የተመለከተ ጥናት በ2022 አድርገዋል።
ማታየር እንደሚሉት ከሙቀት መጨመር ጋር ተያይዞ በሰራተኞች ላይ የሚያጋጥመው ህመም እና ከስራ መቅረት እየጨመረ ይገኛል።
ጥናቱ በ2030 በአለም አቀፍ ደረጃ ከጠቅላላው የስራ ስአት 2 ነጥብ 2 በመቶው በሙቀት መጨመር ምክንያት እንደሚባክን ማመላከቱንም ያነሳሉ።
ይህም የ80 ሚሊየን ሰዎች የሙሉ ጊዜ ስራን ያህል በሙቀት መጨመር ምክንያት ይባክናል ማለት ነው ይላሉ።
በ1955 280 ቢሊየን ዶላር የኢኮኖሚ ኪሳራ ያደረሰው የአየር ንብረት ለውጥ፥ በ2030 ከ2 ነጥብ 4 ትሪሊየን ዶላር በላይ ኪሳራን እንደሚያስከትል መተንበዩንም ነው ያብራሩት።
በዚህም በተለይ የደቡብ እስያ፣ የምዕራብ አፍሪካ እና የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት ክፉኛ ተጎጂ ይሆናሉ ብለዋል።