ኦስትሪያ፣ ስዊዘርላንድ እና ፈረንሳይ ከፍተኛ የሙቀት መጠን የተመዘገበባቸው ሀገራት ናቸው
አውሮፓ በጥቅምት ወር ከፍተኛውን ሙቀት ማስተናገዷ የአውሮፓ ህብረት የኮፐርኒከስ የአየር ንብረት ለውጥ አገልግሎት አስታውቋል፡፡
የሙቀት መጠኑ ከ1991 እስከ 2020 ከነበረው የ2 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ እንደሆነም ነው የኤኤፍፒ ዘገባ የሚያመለክተው፡፡
የአየር ንብረት ተቆጣጣሪው እንደ ኦስትሪያ፣ ስዊዘርላንድ እና ፈረንሳይ የመሳሳሉ የምዕራብ አውሮፓ ሀገራት ከፍተኛ የሙቀት መጠን የተመዘገበባቸው ናቸውም ብሏል፡፡
የአውሮፓ ህብረት የኮፐርኒከስ የአየር ንብረት ለውጥ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ሳማንታ በርገስ "የአየር ንብረት ለውጥ አስከፊ መዘዞች ዛሬ ላይ እያየነቻው ነው እናም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ በኮፕ-27 ላይ በፓሪስ ስምምነት መሰረት የልቀት መጠንን ወደ 1.5 ዲግሪ ሴልሺየስ ለማውረድ ወሳኝ እርምጃ ያስፈልጋል" ብለዋል፡፡
በአብዛኛዎቹ የደቡባዊ አውሮፓ እና የካውካሰስ አካባቢዎች ከአማካይ ሁኔታዎች የበለጠ ደርቀው መታየታቸው የአውሮፓ ህብረት የኮፐርኒከስ የአየር ንብረት ለውጥ አገልግሎት በመግለጫው አስታውቋል።
በተጨማሪም "በአብዛኛው በሰሜን አሜሪካ፣ በአፍሪካ ቀንድ፣ ሰፋፊ የሩሲያ ክፍሎች፣ መካከለኛው እስያ እና ቻይና እንዲሁም በደቡብ አሜሪካ በርካታ ቀጠናዎች ደረቀዋል" ብሏል።
የተባበሩት መንግስታት የዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት እኁድ እንዳስታወቀው የአሁኑ ትንበያ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ የሚመዘገበው የሙቀት መጠን ከ2015 በፊት ከየትኛውም አመት የበለጠ ሞቃት ይሆናል፡፡
በዓለም ሙቀት መጨመር ምክንያት የባህር ከፍታ መጨመር፣ የበረዶ ግግር መቅለጥ፣ ከባድ ዝናብ፣ የሙቀት ሞገዶች መፋጠን መቻላቸውንም ነው የገለጸው ተቋሙ።
ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ጀምሮ ምድር ከ1 ነጥብ 1 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ ሞቃለች፣ ከዚህ ግማሽ ያህሉ ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ የተከሰቱ ናቸው።