የአየር ንብረት ለውጥ ዘላቂ የልማትን እያደናቀፈ እንደሆነ ተገለጸ
እስያ እና አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ እየተጎዱ ያሉ አህጉራት ናቸው ተብሏል
በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ የሚደረገው ስደት እንዲጨምር ማድረጉም ተገልጿል
የአየር ንብረት ለውጥ ዘላቂ የልማትን እያደናቀፈ እንደሆነ ተገለጸ።
የአየር ንብረት ለውጥ ተመድ ባስቀመጠው የዘላቂ ልማት ግቦች እንዳይሳኩ እንቅፋት በመፍጠር ላይ እንደሆነ ተገልጿል።
የአፍሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና አውሮፓ ሀገራት መሪዎች በሮም ጣልያን በአየር ንብረት ለውጥ እና ተያያዥ ጉዳቶች ዙሪያ መክረዋል።
በዚህ ጉባኤ ላይ እንደተገለጸው የአየር ንብረት ለውጥ እያደረሰ ያለው ጉዳት ዓለም አቀፋዊ ቢሆንም አፍሪካ እና እስያ የበለጠ ተጎጂ መሆናቸው በመድረኩ ላይ ተገልጿል።
የአየር ንብረት በዓለም አቀፍ ደረጃ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስም በፈረንጆቹ 2015 በተካሄደው የፓሪስ ጉባኤ ላይ የተወሰነውን ወደ ተግባር መቀየር እንዳለበትም ተገልጿል።
በአፍሪካ እና በእስያ እየደረሰ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ወደ አውሮፓ ለመግባት የሚሞክሩ ስደተኞችን ቁጥር እንዲጨምር አድርጓልም ተብሏል።
በፓሪሱ ጉባኤ ላይ የተወሰኑ የአየር ንብረት ለውጥ ውሳኔዎች እንዲተገበሩ የፊታችን ሕዳር በዱባይ የሚካሄደው ኮፕ28 መድረክም ትልቅ አቅም እንደሚሆን ተገልጿል።
የተባበሩት አረብ ኢምሬት የኢንዱስትሪ ሚንስትር እና የኮፕ28 ጉባኤ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር ሱልጣን አልጃቢር በሮም ባደረጉት ንግግር የአየር ንብረት ለውጥ መደበኛ ያልሆነ ስደት እንዲጨምር በማድረግ ላይ ነው ብለዋል።
የተመድ ኮፕ28 አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ዓለማችንን ከከፋ ጉዳት መጠበቅ የሚያስችል ውሳኔዎች እና ትግበራዎችን የሚጀመሩበት እንደሚሆንም ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰዋል።