ጃፓን ለኮፕ28 የአየር ንብረት ጉባኤ ድጋፍ እንደምታደርግ ገለጸች
ጃፓን እና አረብ ኢምሬት በ2050 የካርበን ልቀትን ዜሮ የማድረስ ተመሳሳይ ግብ አላቸው
ኮፕ28 ጉባኤ የፊታችን ሕዳር በአረብ ኢምሬት አስተናጋጅነት ይካሄዳል
ጃፓን ለኮፕ28 የአየር ንብረት ጉባኤ ድጋፍ እንደምታደርግ ገለጸች።
የተባበሩት አረብ ኢምሬት 28ኛው የዓለም አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን ለማዘጋጀት በዝግጅት ላይ ስትሆን ጉባኤው የፊታችን ሕዳር ወር ይካሄዳል።
ሀገሪቱ ዶክተር ሱልጣን አጃቢርን የጉባኤው ፕሬዝዳንት አድርጋ የሾመች ሲሆን ዝግጅቶች በመጠናቀቅ ላይ እንደሆነም ሀገሪቱ ገልጻለች።
የተለያዩ የዓለም ሀገራትም ለአረብ ኢምሬት ድጋፋቸውን በመግለጽ ላይ ሲሆኑ ጃፓን አንዷ ናት።
በአቡዳቢ የጃፓን አምባሳደር አኪዎ ኢሱማታ ከአልዐይን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት የተባበሩት አረብ ኢምሬት እና ጃፓን በ2050 የበካይ ጋዝ ልቀት መጠንን ዜሮ የማድረስ የጋራ ግብ አላቸው ብለዋል።
አምባሳደር ኢሱማታ እክለውም ጃፓን እና አረብ ኢምሬት ባለፉት 50 ዓመታት በትብብር ያከናወኗቸው አያሌ አጀንዳዎች እንደነበሩም ተናግረዋል ።
ሁለቱ ሀገራት በቀጣዮች 50 ዓመታት የማይተባበሩባቸው የሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፍ አጀንዳዎች አይኖሩም ሲሉም አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።
የጃፓኑ ጠቅላይ ሚንስትር ፉሚዮ ኪሽዳ አረብ ኢምሬትስን መጎብኘታቸው የሁለቱ ሀገራት ትብብር የበለጠ እንዲያድግ ትልቅ አቅም ይሆናልም ብለዋል አምባሳደር ኢሱማታ።
አምባሳደሩ አክለውም የአቡዳቢ እና ቶኪዮ ትብብር ለብዙ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ነው ያሉት አምባሳደሩ ማሳካት የሚፈልጓቸው አጀንዳዎች ተመሳሳይ ናቸውም ብለዋል።
የታዳሽ ሀይል ልማት በቴክኖሎጂ እና ፈጠራ የታጀበ ማድረግ ዋነኛው የሁለቱ ሀገራት ፍላጎት መሆኑን የገለጸት አምባሳደሩ ትብብራቸው እና አብሮ መስራቱ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
የሁለቱ ሀገራት ከነዳጅ ውጪ ያለው የንግድ እና ኢንቨስትመንት መጠን ከ18 ቢሊዮን ዶላር በላይ መድረሱም ተገልጿል።