የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በፀጥታው ም/ቤት ተለዋጭ አባል ሆና ተመረጠች
ዩኤኢ በለመደችው የዓለም አቀፍ ተሳትፎ እና የትብብር መንፈስ እንደምትሰራ ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ ገልጸዋል
ዩኤኢ በለመደችው የዓለም አቀፍ ተሳትፎ እና የትብብር መንፈስ እንደምትሰራ ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ ገልጸዋል
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለሁለት ዓመታት በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም / ቤት ውስጥ የተለዋጭ አባልነት መቀመጫ እንዲኖራት ተመርጣለች፡፡
“የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዛሬ ሰኔ 4 ቀን 2013 ዓ.ም ዩኤኢን ለ 2022-2023 የፀጥታው ም/ቤት ከአምስት አባላት አንዷ እንድትሆን መርጧል” ሲሉ የአቡዳቢ ዘውዳዊ ልዑል እና የዩኤኢ ጦር ምክትል ጠቅላይ አዛዥ ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ በትዊተር አድራሻቸው ገልጸዋል፡፡ “ቁርጠኛ ዲፕሎማቶቻችን ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከተመሠረተችበት 1971 ጀምሮ የተመራችበትን የዓለም አቀፍ ተሳትፎ እና የትብብር መንፈስ እንደሚከተሉ ቃል እንገባለን” ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የስካይ ኒውስ መረጃ እንደሚያመለክተው ዩኤኢ ለፀጥታው ም / ቤት ተለዋጭ አባልነት የተመረጠችው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔን 179 ድምጽ በማግኘት ነው፡፡
ሀገሪቱ እ.ኤ.አ. በመስከረም ወር 2020 መጨረሻ ላይ ነበር ከ 2022 እስከ 2023 ባለው ጊዜ ውስጥ ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም/ቤት ቋሚ ያልሆነ መቀመጫ እጩ መሆኗ የታወቀው፡፡
ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በተጨማሪ አልባኒያ፣ ብራዚል፣ ጋቦን እና ጋናም በተለዋጭ አባልነት ተመርጠዋል፡፡ እነዚህ አምስት ሀገራት ኤስቶኒያ፣ ኒጀር፣ ቱኒዚያ፣ ቬትናም እና ሴንት ቪንሴንት ኤንድ ዘ ግሬናዲንስን በመተካት ም/ቤቱን የሚቀላቀሉ ናቸው፡፡
የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም/ቤት አምስት ቋሚ አባላትን (አሜሪካ ፣ ሩሲያ ፣ ቻይና ፣ ብሪታንያ እና ፈረንሣይ) እና 10 ቋሚ ያልሆኑ አባላትን ፣ ማለትም በድምሩ 15 አባላትን ያቀፈ ነው፡፡