140 ሚሊየን ሰዎች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ስደተኛ ይሆናሉ - የአለም ባንክ
በዚህ ችግር የአፍሪካ፣ ላቲን አሜሪካ እና ደቡብ እስያ ሀገራት ዜጎች ይበልጥ ተጋላጭ ይሆናሉ ተብሏል
በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ስደተኛ የሚሆኑ ሰዎችን ደህንነት የሚጠብቅ አለማቀፍ ህግ የለም
ፓኪስታን ባለፈው አመት በነሃሴ ወር የደረሰባት የጎርፍ አደጋ የበርካቶችን ህይወት አመሳቅሏል።
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ “የአየር ንብረት ለውጥ ጭፍጨፋ” ሲሉ የገለጹት አደጋ ከ1 ሲህ 700 በላይ ሰዎችን ለሞት ዳርጓል።
ከ14 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚገመት ንብረት ያወደመው የጎርፍ አደጋ 8 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎችንም አፈናቅሏል።
ትምህርት ቤቶችን ወደ ጊዜያዊ መጠለያ ካምፕ ያስቀየረው አደጋ ሰለባ ከሆኑት መካከል ሱማን የተሰኘችው የ22 አመት ወጣት ቤታቸው በጎርፍ ከተወሰደ በኋላ አስቸጋሪ ህይወት እያሳለፉ መሆኑን ለአል ዐይን ኒውስ ተናግራለች።
እንደ ሱማን ሁሉ በአደጋው ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች “የአየር ንብረት ለውጥ ተፈናቃዮች” ይሰኛሉ፤ የተፈጥሮ አደጋው ከሀገራቸው ሲያስወጣቸው ደግሞ “የአየር ንብረት ለውጥ ስደተኞች” ይባላሉ።
የአለም ባንክ ጥናት እንደሚያሳየው የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችሉ ስራዎች በሚገባ ካልተከናወኑ 140 ሚሊየን ሰዎች የአየር ንብረት ለውጥ ስደተኛ ይሆናሉ።
በዚህ ችግር ክፉኛ የሚጎዱት ደግሞ የአፍሪካ፣ ላቲን አሜሪካ እና ደቡብ እስያ ሀገራት ዜጎች ናቸው ይላል ጥናቱ።
በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚፈናቀሉና ድንበር አቋርጠው የሚሰደዱ ሰዎች ዘርፈ ብዙ ፈተና እንደሚገጥማቸው ይናገራሉ።
በተለይ በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት የሚሰደዱ ሰዎችን የሚጠብቅ አለማቀፍ ህግ አለመኖሩ ስደተኞቹ በርካታ ችግሮችን እየተጋፈጡ እንዲቀጥሉ ማስገደዱን በማከል።
የምግብ እና መጠጥ አቅርቦት ውስንነት እና በመጠለያ ካምፖች ውስጥ ተጨናንቆ ከመኖር ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ የጤና ችግሮች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎችን እየፈተኑ ስለመሆኑም የአለም ባንክ ጥናት አሳይቷል።
እናም ሀገራት ሚሊየኖችን የሚያፈናቅሉ የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመቀነስ የሚያስችሉ ስራዎችን እንዲያከናውኑ አሳስቧል።