ከባድ ሙቀትና ወበቅ በሰው ልጆች ላይ ምን አይነት የጤና እክል እያደረሰ ነው?
የፔን ዩኒቨርሲቲ ያደረገው ጥናት ከባድ ወበቅ የልብ ደህንነትን እያናጋ መሆኑን አሳይቷል
በአየር መበከል ምክንያት በሚፈጠሩ ህመሞች በየአመቱ ሚሊየኖች ህይወታቸውን ያጣሉ
ተመራማሪዎች የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን ጉዳት ሲያጠኑ ብዙ ጊዜ በሙቀት መጨመርና የውቅያኖሶች ግግር በረዶ መቅለጥ ላይ ያተኩራሉ።
የአየር ንብረት ለውጥ በሰዎች ጤና ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በዝርዝር የሚዳስሱ ጥናቶች እምብዛም ሲወጡ አይታይም።
በአሜሪካ የፔን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪው ሌሪ ኬኒ በዩኒቨርሲቲው ድረገጽ ይፋ ያደረጉት የጥናት ውጤታቸው ግን የአለም የሙቀት መጨመር በሰው ልጆች ጤና ላይ እያሳደረ የሚገኘውን ተጽዕኖ አሳይቷል።
ፕሮፌሰር ሌሪ በተለይ ከፍተኛ ሙቀት እና ወበቅ የጤና ጠንቅ መሆኑን ያነሳሉ።
የሰው ልጆች በሰውነታቸው የተከማቸን ከፍተኛ ሙቀት የሚያስወግዱት በላብ ነው የሚሉት ተመራማሪው፥ ከፍተኛ ሙቀትና ወበቅ ግን ሰውነታችን በላብ እንዲሞላ እና ውስጣዊ ሙቀትን በላብ ትነት እንዳያስወግድ ያደርገዋል ባይ ናቸው።
ይህም በተፈጥሯዊ መንገድ ሰውነታችን ራሱን የሚያቀዘቅዝበትን ሂደት በማዛባት የጤና እክል ያስከትላል ነው ያሉት በጥናታቸው።
ከላብ ባሻገር ሰውነታችን ከፍተኛ ሙቀትን የሚያቀዘቅዘው ወደ ቆዳችን ደም በማሰራጨት ነው።
“ሙቀትና ወበቅን ለመቋቋም ልባችን ወደ መላ ሰውነታችን ቆዳ ደም ሲረጭ በጊዜ ሂደት ከባድ ጉዳት ማስከተሉ አይቀሬ ነው” ይላሉ ፕሮፌሰር ሌሪ ኬኒ።
በከባድ ሙቀትና ወበቅ ምክንያት የልብ ምት ይበልጥ ከፍ ማለቱ ታዲያ በተለይ አዛውንቶች እና ህጻናት ላይ ተጽዕኖው እንደሚበረታ ያብራራሉ።
በተሽከርካሪዎች ውስጥ ሞተው የሚገኙ ህጻናት የበዙትም በዚሁ ሙቀትን መቆጣጠር የሚያስችል የልብ ሰርአት ማዳበር ካለመቻላቸው ጋር ተያይዞ መሆኑንም ይጠቅሳሉ።
እድሜያቸው የገፋ ሰዎችም የልባቸው ወደ ቆዳ ደም የመርጨት አቅም ስለሚዳከም በልባቸው ላይ ከፍተኛ ጫና ተፈጥሮ ህይወታቸውን እያሳጣቸው እንደሚገኝ በማከል።
የአለማቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ፓኔል (አይፒሲሲ) ጥናትም ከባድ ሙቀትና ወበቅ ዘርፈብዙ የጤና እክሎችን እንደሚያመጣ ያሳያል።
በአውሮፓ ሀገራት የበርካቶችን ህይወት እየቀማ ያለው የከባቢ አየር ሙቀት መጨመር በአዕምሮ ጤና ላይ ጥቁር አሻራውን እያኖረ እንደሚገኝ ነው ጥናቱ ያመላከተው።
ድብርት እና ጭንቀትን የሚያስከትለው ከባድ ሙቀትና ወበቅ ራስን ለማጥፋት ምክንያት እየሆነ መምጣቱንም እንዲሁ።
የልብ፣ ኩላሊት እና የአስም በሽታን ጨምሮ በአየር ብክለት የሚመጡ የጤና እክሎች በ2019 ብቻ የ4 ሚሊየን ሰዎችን ህይወት መቅጠፋቸውን ጥናቱ አመላክቷል።