በከባድ ሙቀት ምክንያት ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ተገለጸ
ባለፈው አመት ከ62 ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው ከባድ ሙቀትና ወበቅ በዚህ አመትም ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ነው ተብሏል
በአውሮፓ እና አሜሪካ የተለያዩ ከተሞች ክብረወሰን የሆነ ሙቀት እየተመዘገበ ነው
በአሜሪካ እና ህንድ ከባድ ሙቀት እና ደራሽ ጎርፍ ከባድ ጉዳት አድርሰዋል።
ሁለቱን ሀገራት ለአብነት አነሳን እንጂ በመላው አለም የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለው ጉዳት ድንገቴነቱ እና ድግግሞሹ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አልሄደም።
በ2022 በአውሮፓ ሀገራት ብቻ ከ62 ሺህ በላይ ሰዎች በከባድ ሙቀት ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል።
በአሁኑ ወቅትም በአውሮፓ እና እስያ ሀገራት በሙቀት፣ ጎርፍ እና አውሎ ንፋስ ምክንያት ህይወታቸውን እያጡ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም።
የመንግስታቱ ድርጅት ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫም “አለም ለከባድ ሙቀት እና ወበቅ” ልትዘጋጅ ይገባል ብሏል።
የአለም ከፍተኛው የሙቀት መጠን በዚህ አመት ሃምሌ ወር መመዝገቡ የሚታወስ ሲሆን፥ ጣሊያንም ክብረወሰኑን ከቀናት በፊት አሻሽላዋለች።
በደቡባዊ ጣሊያን የምትገኘው ታረንት ከተማ 46 ዲግሪ ሴልሺየስ ሙቀት በማስመዝገብ የአውሮፓን ሪከርድ ይዛለች።
በአሜሪካም የአሪዞናዋ ፎኒክስ 43 ዲግሪ ሴልሺየስ የሆነ ከባድ ሙቀት ተመዝግቧል።
በሰሜን አሜሪካ፣ እስያ እና ደቡብ አፍሪካ ሀገራት በዚህ ሳምንት አማካይ የከባቢ አየር ሙቀት 40 ዲግሪ ሴልሺየስ እንደሚደርስም ነው የአለም የሜትሮሎጂ ድርጅት ትንበያ የሚያሳየው።
ድርጅቱ በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች እየታየ ያለው ከባድ ሙቀትና ደራሽ ጎርፍ እየጨመረ የሚሄድ እንጂ የሚቀንስ አይደለም ብሏል።
በድርጅቱ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ጆን ናይርን ከጀኔቫ በሰጡት መግለጫ፥ አለማችን እያስተናገደችው ያለው ሙቀት በ1980ዎቹ ከነበረው በስድስት እጥፍ ጭማሪ ያሳየ ነው ማለታቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ አስነብቧል።
ከአሜሪካ እስከ ጣሊያን፤ ከስፔን እስከ ጓቲማላ በርካታ ሀገራትን እየፈተነ ያለው ሙቀት በሰዎች ጤና ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖም ከፍተኛ መሆኑን ነው አማካሪው ያነሱት።
የ2023 ሪፖርት አመቱ ሲጠናቀቅ ይፋ የሚደረግ ቢሆንም በየሀገራቱ በሙቀቱ መጨመር ምክንያት ህይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሄዱንም በማከል።
ባለፈው አመት በተመሳሳይ የአየር ንብረት ለውጥ ዳፋ ምክንያት በአውሮፓ ብቻ 62 ሺህ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።
ከከባድ ሙቀትና ወበቁ ባሻገር በተለያዩ ሀገራት እየተከሰቱ የሚገኙ የእሳት አደጋዎችም ዜጎችን ለህልፈትና መፈናቀል እየዳረጉ ነው።
በግሪክ አቴንስ ከ1 ሺህ 200 በላይ ሰዎችን ያፈናቀለ ሰደድ እሳትን ጨምሮ ካናዳ፣ አሜሪካ እና ሌሎች ሀገራት በመሰል ችግር እየተፈተኑ ይገኛሉ።