በግርዛት ምክንያት የተጎዳን የሴት ብልት አካል ማስመለስ እንደሚቻል ያውቃሉ?
በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት በሴት ህጻናት ላይ በሚፈጸም ግርዛት ምክንያት ለእድሜ ልክ ጉዳት እየተዳረጉ ነው
በከባድ ግርዛት ምክንያት የብልት አካላቸውን ላጡ ሴቶች የቀዶ ጥገና ሕክምና መስጠት ተጀምሯል
በግርዛት ምክንያት ያጡትን የሴት ብልት አካል ማስመለስ እንደሚቻል ያውቃሉ?
ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ የዓለማችን ሀገራት በሴት ልጅ ላይ ግርዛት የሚፈጸም ሲሆን ጉዳቱ እንደ ሀገሩ ይለያያል፡፡
አፍሪካ ከባድ የሴት ልጅ ግርዛት የሚፈጸምበት አህጉር ሲሆን በጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ከባድ የሚባል እና ሴቶችን ለእድሜ ልክ ስቃይ የሚዳርግ ነው ተብሏል፡፡
ከሰሞኑ ሻምሳ ሻራዌ የምትባል እና በስደት በእንግሊዝ ሀገር የምትኖር አንድ ሶማሊያዊት በቲክቶክ ገጿ በስድስት ዓመቷ በተፈጸመባት ከባድ ግርዛት ምክንያት ለእድሜ ልክ ስቃይ መዳረጓን አጋርታለች፡፡
ይህች ሶማሊያዊት በማህበራዊ ሚዲያ “ቂንጥሬ ይመለስልኝ” የሚል የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ መክፈቷን ቢቢሲ የበዘገባው ላይ ጠቅሷል፡፡
ሻምሳ ሻራዌ እንዳለችው “ሳንፈልግ እና ሳንመርጥ በተፈጸመብን ጉዳት እድሜ ልካችን ስንጎዳ መኖር የለብንም” ያለች ሲሆን ድርጊቱ መቆም አለበት ስትል ጥሪ አቅርባለች፡፡
ሻምሳ ሻራዌ በህጻንነቷ በተፈጸመባት ግርዛት የብልቷ የታችኛው እና ላይኛው ከንፈርን ጨምሮ ቂንጥሯ እንደተቆረጠባት የተናገረች ሲሆን ስለ ጉዳዩ ያብራራችበት ተንቀሳቃሽ ምስል በ18 ደቂቃ ውስጥ ከ12 ሚሊዮን በላይ ተመልካች አግኝቷል፡፡
ሻምሳ የሚሊዮን ሴቶችን ጉዳት ይዛ ቃሉን ለመጥራት ሳትሸማቀቅ ወደ አደባባይ ማውጣቷ ከበርካቶች ድጋፍ የተቸራት ሲሆን የበጎ አድራጎት እና ህክምና ባለሙያዎች ድጋፍ እንደሚያደርጉላት ቃል ገብተውላታል፡፡
ይህን ተከትሎ በግርዛት ምክንያት ስቃይ ውስጥ ያሉ ሴቶችን ለመታደግ የህክምና ተቋማት እና ባለሙያዎች በተለይም ደረጃ ሶስት የሚባለው ከባድ ግርዛት ምክንያት ተብሎ የሚጠቀስ ሲሆን የዚህ ሰለባ የሆኑ ሰዎች ወሲብ ማድረግ፣ መደሰት እና ማማጥ ለከባድ ህመም ይዳርጋቸዋል ተብሏል፡፡
በግርዛት ምክንያት ህይወታቸውን ከስቃይ ወደ ደስታ ለመለወጥ በተወሰኑ የዓለማችን ሀገራት የቀዶ ህክምናው እየተደረገ እንደሆነ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ህክምናው በግርዛት ወቅት የተጎዳ ብልት ወደ ተፈጥሯዊ ባህሪው እንዲመለስ ማለትም የደም ዝውውር እንዲኖር፣ ፈሳሽ እንዲያመነጭ እንዲሁም በወሲብ እና ምጥ ወቅት እንዲለጠጥ የሚያደርግ ነው ተብሏል፡፡
አሁን ላይ ይህ የብልት ቀዶ ጥገና ህክምና በአውሮፓ በጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ቤልጂየም፣ ፊንላንድ፣ ስዊድን እና ስዊዘርላንድ በመሰጠት ለይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በአፍሪካ ደግሞ በጎረቤት ሀገር ኬንያ እና ግብጽ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች በኩል ህክምናው ይሰጣል የተባለ ሲሆን የህክምና ዋጋውም ከ1 ሺህ ዩሮ ጀምሮ እንደሆነ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
የተጎዳ ብልት አካል ቀዶ ሕክምና ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የተደረገው በፈረንሳው ዝነኛ ሐኪም ዶክተር ፒሬ ፎልድስ አማካኝነት በፈረንጆቹ 2004 ላይ ነበር፡፡
ኢትዮጵያ የሴት ልጅ ግርዛትን ጨምሮ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን እስከ ፈረንጆቹ 2025 ድረስ ሙሉ ለሙሉ አስቆማለሁ በሚል ከ15 ዓመት በፊት የቃል ኪዳን ሰነድ መፈረሟ ይታወሳል፡፡