ከስታዲየም መግቢያ ትኬት ከፍተኛ ገቢ ያስገቡ ክለቦች
ከትኬት ሽያጭ ከፍተኛ ገቢ ካገኙት 10 የአውሮፓ ክለቦች ውስጥ ስድስቱ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፉ ናቸው

የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ባለፈው አመት ከትኬት ሽያጭ 1 ቢሊየን ዩሮ የሚጠጋ ገቢ አግኝተዋል
ከ20ዎቹ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች 19ኙ ከ2024/25 የውድድር አመት በፊት የስታዲየም መግቢያ ትኬት ዋጋ ላይ ጭማሪ አድርገዋል።
ክለቦች ለአዛውንቶች እና ታዳጊዎች ይደረግ የነበረ ቅናሽን መሰረዛቸው ቁጣ ቀስቅሷል።
የትኬት ዋጋ መናገር የተለያዩ ክለብ ደጋፊዎችን በአንድ አሰልፎ የእግርኳስ ደጋፊዎች ማህበር "ታማኝነታችን መበዝበዛችሁን አቁሙ" የሚል ዘመቻ እንዲጀመር ማድረጉን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።
ክለቦች ደግሞ የስራ ማስኬጃ ወጪዎች መጨመር እና የፍትሃዊ ፉክክር ህጎችን ለትኬት ዋጋው ማደግ በምክንያትነት ያነሳሉ።
የአውሮፓ እግርኳስ ማህበር የአህጉሩን ክለቦች የ2024 የፋይናንስ እና ኢንቨስትመንት ሪፖርት ይፋ ሲያደርግ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ከስታዲየም መግቢያ ትኬት 1 ቢሊየን ዩሮ የሚጠጋ (830 ሚሊይን ፓውንድ) ገንዘብ ማግኘታቸውን አመላክቷል።
የፕሪሚየር ሉጉ ክለቦች በየአመቱ በ10 በመቶ እየጨመረ የመጣው የትኬት ገቢያቸው ከስፔን ላሊጋ (481 ሚሊየን ፓውንድ) እና ከጀርመን ቡንደስሉጋ (430 ሚሊየን ፓውንድ) በእጥፍ እንደሚልቅም ጠቁሟል።
ከስታዲየም መግቢያ ትኬት ከፍተኛ ገቢ ከሚያገኙት 10 የአውሮፓ ክለቦች ስድስቱ የእንግሊዝ ናቸው።
በ2023/24 የውድድር አመት 153 ሚሊየን ፓውንድ ያስገባው የስፔኑ ሪያል ማድሪድ ቀዳሚው ክለብ ነው፤ የፈረንሳዩ ፒኤስጂ በ139 ሚሊየን ፓውንድ ይከተላል።
የአውሮፓ እግርኳስ ማህበር ሪፖርት የስታዲየም ማስፋፊያ እና አዳዲስ አገልግሎቶች በፓሪስ ሴንት ጀርሜን፣ ባየር ሙኒክ፣ ሊቨርፑል እና ማንቸስተር ሲቲ ከ2009 ወዲህ ከትኬት የሚገኘውን ገቢ በእጥፍ ማሳደጉን አመላክቷል።