
አስሩ ቀዳሚ ምርት ላኪ ሀገራት በድምሩ 12 ትሪሊየን ዶላር የሚጠጋ ዋጋ ያላቸው ምርቶችን ወደተለያዩ ሀገራት ልከዋል
የወጪ ንግድ የአንድ ሀገር የኢኮኖሚ እድገት ማሳያ ነው።
ምርቶቻቸውን ለበርካታ ሀገራት በመላክ በቢሊየን ዶላር የሚያስገቡ ሀገራት የአለም የገበያ ስርአትን ይቆጣጠራሉ።
በአለማችን ሁለተኛዋ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ሀገር ቻይና ከወጪ ንግድ ከፍተኛውን ገቢ በማስገባት ቀዳሚዋ ሀገር ናት። ግሎባል ስታስቲክስ የአለም የንግድ ድርጅትን ዋቢ አድርጎ ባወጣው ዘገባ ቻይና በ2023 3.38 ትሪሊየን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ለውጭ ገበያ አቅርባለች።
ቤጂንግ የኤሌክትሮኒክስ፣ የጨርቃ ጨርቅ፣ ብረትና ሌሎች ምርቶችን በመላክ ከፍተኛ ገቢ ታስገባለች።
እንደ ሁዋዊ፣ ሻኦሚ፣ ሌኖቮ እና ሌሎች አለማቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መገኛዋ ቻይና ከ120 በላይ ወደሚሆኑ ሀገራት ምርቶቿን በመላክ በአለማቀፉ ገበያ ጉልህ ድርሻ ይዛለች።
አሜሪካ ከቻይና በመቀጠል ሁለተኛዋ የወጪ ንግድ ተጠቃሚ ሀገር ስትሆን ከ2 ትሪሊየን ዶላር በላይ የሚያወጡ ምርቶችን ወደተለያዩ ሀገራት ልካለች።
ዋሽንግተን የቦይንግ አውሮፕላኖች፣ ተሽከርካሪዎች፣ መድሃኒቶች እና የግብርና ምርቶችን በስፋት ለአለም ገበያ እንደምታቀርብ ተገልጿል።
1 ነጥብ 7 ትሪሊየን ዶላር የሚጠጋ ዋጋ ያላቸው ምርቶችን የላከችው አውሮፓዊቷ ጀርመን ደግሞ ሶስተኛን ደረጃ ይዛለች። ኔዘርላንድስ፣ ጃፓን፣ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሜክሲኮና ሲንጋፖር ከ4 እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
አስሩ ቀዳሚ ምርት ላኪ ሀገራት በድምሩ 12 ትሪሊየን ዶላር የሚጠጋ ዋጋ ያላቸው ምርቶችን ወደተለያዩ ሀገራት ልከዋል።
በአንጻሩ በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገችው አፍሪካ እሴት ጨምራ ምርቶችን ወደ ወጪ ሀገራት በማቅረብ ረገድ አሁንም በርካታ ማነቆዎች ይዘዋታል።
የመሰረተ ልማት አለመሟላት፣ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ የኢንዱስትሪ አለመስፋፋትና ሌሎች ምክንያቶች አህጉሪቱ በወጪ ንግድ ደረጃ ከአለም ሀገራት ግርጌ ላይ አስቀምጠዋታል።
የአፍሪካ ሀገራት በደቡብ አፍሪካ እና ናይጀሪያ ከታየው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በመማርና በአምራች ዘርፉ በስፋት በመስራት የሸቀጦች መራገፊያ ከመሆን ወደ ላኪነት መሸጋገር ሊጀምሩ እንደሚገባ የቢዝነስ ኢንሳይደር ዘገባ ጠቁሟል።