ለዩክሬን ከፍተኛ ድጋፍ ያደረጉ ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
ከጥር 2022 ጀምሮ እስከ ታህሳስ 2024 ድረስ በተለያዩ ዘርፎች ዩክሬን በመቶ ቢሊየን ዶላሮች ድጋፍ አግኝታለች

አሜሪካ በወታደራዊ ፣ በሰብአዊ እና በገንዘብ ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ ቀዳሚዋ ናት
ምዕራባውያን እና ሌሎች ሀገራት የዩክሬን እና ሩስያ ጦርነት በ2022 ከተጀመረ አንስቶ ከዩክሬን ጎን በመሰለፍ በሰብዓዊ ፣ በወታደራዊ እና በገንዘብ ድጋፍ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ፈሰስ አድርገዋል፡፡
ዩክሬን የሩስያን ውጊያ ለመከላከል ከተለያዩ ሀገራት እና ድርጅቶች ከ280 ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ እንደተደረገላት ስታቲስታ ባወጣው መረጃ ጠቁሟል፡፡
አሜሪካ ከየትኛውም ሀገር በበለጠ ለዩክሬን ሁለንተናዊ ድጋፍ በማድረግ ቀዳሚዋ ስትሆን በገንዘብ ሲተመን 119 ቢሊየን ዶላርን ይሻገራል፡፡
በአጠቃላይ የአውሮፓ ህብረት 138 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ፣ ወታደራዊ እና ሰብአዊ ዕርዳታ መስጠቱን ዘገባዎች አመልክተዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት በጀርመኑ ኬል ኢኮኖሚ ጥናት ተቋም ይፋ በሆነው ሪፖርት ዋሽንግተን 64 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ ዕርዳታ፣ 46 ቢሊዮን ዶላር የፋይናንስ ዕርዳታ እና 3.5 ቢሊዮን ዶላር ሰብዓዊ ዕርዳታ ሰጥታለች።
የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ ለዩክሬን ያደረገው ከፍ የሚለው ድጋፍ የገንዘብ ሲሆን ይህም 68 ቢሊየን ዶላር ይጠጋል ፤ 53 ቢሊየን ዶላር ደግሞ ወታደራዊ ወጪ አድርጓል።
ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባሉት ሶስት አመታት ውስጥ ከአውሮፓ ህብረት የተገኘው የሰብአዊ እርዳታ 17 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።
በሩስያ በኩል ጦርነት ያስከተለውን ወጪ ለማስላት አስቸጋሪ ቢሆንም ሞስኮ ለጦርነቱ ከ211 ቢሊዮን ዶላር በላይ ስለማውጣቷ ይገመታል፡፡
ቀጥተኛ ወታደራዊ ድጋፍን በተመለከተ ፖላንድ 354 ታንኮችን ለዩክሬን ለግሳለች ፣ ኔዘርላንድ 104 ፣ ዴንማርክ 77 እና አሜሪካ 76 ታንኮችን ሰጥተዋል፡፡
በሶስት አመቱ ጦርነት ለዩክሬን ከፍተኛ ጥቅል ድጋፎችን በማድረግ አሜሪካ ፣ የአውሮፓ ሀብረት ፣ ጀርመን ፣ ብሪታንያ ፣ ጃፓን እና ካናዳ በደረጃ ተቀምጠዋል፡፡