ኮካኮላ ኩባንያ የፕላስቲክ ምርቶችን ለመጠቀም እንደሚገደድ ገለጸ
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ የአሉምኒየም እና ብረት ምርቶች ላይ የ25 በመቶ ቀረጥ ጥለዋል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/12/258-160409-coke-brandz-article-cover_700x400.jpg)
ኮካኮላ ኩባንያ የፕሬዝዳንቱ ውሳኔ የአሉምኒየም ምርቶችን ዋጋ እንደሚያንር አስታውቋል
ኮካኮላ ኩባንያ የፕላስቲክ ምርቶችን ለመጠቀም እንደሚገደድ ገለጸ።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በያዝነው ሳምንት ላይ ካሳለፏቸው ውሳኔዎች መካከል ወደ አሜሪካ በሚገቡ የብረት እና አሉምኒየም ምርቶች ላይ የጣሉት አዲስ የግብር ቀረጥ ይገኝበታል።
ውሳኔውን ተከትሎም ኮካሎላ ኩባንያ የአሉሚኒየም ምርት ዋጋ ያንራል ሲል አስታውቋል።
ኩባንያው ኪሳራውን ለመቀነስ ሲል የፕላስቲክ ምርቶችን ለመጠቀም እንደሚገደድ የገለጸ ሲሆን ይህም በአየር ንብረት ላይ የራሱን ጉዳት ያደርሳል ብሏል።
የዓለማችን ቁጥር አንድ ለስላሳ መጠጦች አምራች የሆነው ኮካኮላ ኩባንያ ፕላስቲክ ምርቶችን በመጠቀም እና አካባቢን በመበከል ቁጥር አንድ ኩባንያ ነው።
ይህን ስሙን ለማስተካከል በሚልም በየዓመቱ የፕላስቲክ ምርቶችን የመቀነስ እቅድ አውጥቶም ነበር።
ኩባንያው በአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የሚጠቀማቸውን ፕላስቲኮች መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል እና ቀስ በቀስ የፕላስቲክ ምርቶቹን እንደሚቀንስ ገልጾም ነበር።
ይህ በዚህ እንዳለ አዲሱ የዶናልድ ትራምፕ አዲስ የብረት እና አሉምኒየም ምርቶች ቀረጥ የኩባንያውን ወጪ ስለሚያንረው ወደ ፕላስቲክ ምርቶች እንዲመለስ እንዳደረገው ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲሱ የብረት እና አሉምኒየም ምርቶች ቀረጥ በተለይም የታሸጉ እና የተቀነባበሩ ምግቦችን የሚሸጡ ተቋማትን ወጪ እንደሚጨምርባቸውም ተገልጿል።