ሜሲን ለመመልከት ስታዲየም የተገኙ ቻይናውያን የትኬት ወጪያቸው ሊመለስላቸው ነው
አርጀንቲናዊው ኮከብ በሆንግ ኮንግ የወዳጅነት ጨዋታ ላይ አለመሰለፉ የውድድሩን አዘጋጅ 7 ነጥብ 1 ሚሊየን ዶላር ያሳጣዋል ተብሏል
የስምንት ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊው ያስከፋቸውን ደጋፊዎች እንደሚክስ ቢገልጽም ቁጣው እስካሁን አልበረደም
የኢንተር ሚያሚውን አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ ለመመልከት በሆንግ ኮንግ ስታዲየም የተገኙ ቻይናውያን ግማሽ የትኬት ወጪያቸው ሊመለስላቸው ነው።
ሜሲ ክለቡ በየካቲት ወር ከሆንግ ኮንግ 11 ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ሲያደርግ አለመሰለፉና ደጋፊዎቹን ሰላምታ አለመስጠቱ ቁጣ ማስነሳቱ ይታወሳል።
የ36 አመቱ አርጀንቲናዊ በጨዋታው ላይ እንደሚሰለፍ መነገሩን ተከትሎ ከ12 ስአት በላይ ተጉዘው እስከ 600 ዶላር የሚያወጣ ትኬት ገዝተው ስታዲየም የገቡ አድናቂዎቹ የጠበቁትን አላገኙም።
የወዳጅነት ጨዋታውን ያዘጀው ታትለር ኤሽያ “ሜሲ ይሰለፋል ብሎ አጭበርብሮናል፤ በውድ ዋጋ የገዛነው ትኬት ሊመለስ ይገባዋል” የሚሉ ድምጾችም በዚያው በስታዲየም ውስጥ ሲሰሙ ነበር።
በዚህም መሰረት የኢንተርሚያሚ እና ሆንግ ኮንግ 11 ጨዋታን ለመመልከት ስታዲየም የተገኙ 38 ሺህ ቻይናውያን ደጋፊዎቹ ግማሽ የትኬት ወጪያቸው እንዲመለስላቸው ተወስኗል።
የትኬት ወጪያቸው ተመላሽ የሚደረግላቸው ሰዎች ጉዳዩን ወደ ህግ አካል መውሰድ ወይም ክስ መመስረት እንደማይችሉም ነው ታትለር ኤሽያ ያስታወቀው።
ድርጅቱ ያሳለፈው ውሳኔ ከ7 ነጥብ 1 ሚሊየን ዶላር በላይ እንደሚያሳጣው ተገልጿል።
በሜሲ ድርጊት የተበሳጨው የሆንግ ኮንግ መንግስት የውድድሩ አዘጋጅ በፍጥነት የትኬት ዋጋ ተመላሽ እንዲያደርግ ማሳሰቡ ይታወሳል።
የቻይና መንግስት አቋም የሚንጸባረቅበት ቻይና ዴይሊ ሜሲ በሆንግ ኮንግ የጡንቻ ጉዳት ገጥሞኛል በሚል ሳይሰለፍ ከሶስት ቀናት በኋላ በጃፓን መጫወቱ ተጫዋቹና ክለቡ ልዩ ፖለቲካዊ ፍላጎት አላቸው የሚል የሴራ ትንታኔ ውስጥ እንዲገባ ማድረጉም አይዘነጋም።
የስምንት ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊው ግን ለቻይናውያን የተለየ ፍቅር እንዳለው በመግለጽ የሚቀርብበትን ወቀሳ ውድቅ አድርጓል።
የሁዋዌ፣ ቼሪ፣ ቴንሴንት እና ሌሎች ግዙፍ የቻይና ታዋቂ ምርቶችና አገልግሎቶች አስተዋዋቂው ሜሲ በመጋቢት ወር ወደ ቻይና ሲመለስ ያስከፋቸውን ደጋፊዎች ለመካስ እንደሚሰራ ተናግሯል።
የቻይና ባለስልጣናት የአርጀንቲና ክለቦች በዚህ ወር በቻይና ሊያደርጓቸው የነበሩ ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን መሰረዛቸው ግን ቅራኔው እስካሁን እንዳልበረደ ያሳያል ብሏል ቢቢሲ በዘገባው።