ስኳር የበዛባቸው ለስላሳ መጠጦች የሚዘወተርባቸው 10 ሀገራት
የአሜሪካው ተፍትስ ዩኒቨርሲቲ በ185 ሀገራት ያደረገው የዳሰሳ ጥናት ስኳር ያላቸው ለስላሳ መጣጦች ፍጆታ እያደገ መምጣቱን አሳይቷል
ስኳር የበዛባቸው መጠጦች ለልብ እና የስኳር በሽታዎች የማጋለጥ እድላቸው ከፍ ያለ ነው
ስኳር ያላቸው ለስላሳ መጠጦችን በብዛት መጠቀም በሰው ልጆች ጤና ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖን የተመለከቱ ጥናቶች በተደጋጋሚ ወጥተዋል።
የስኳር እና ልብ ህመም፣ የጥርስ መበስበስ እና ከልክ ያለፈ ውፍረትን ጨምሮ የተለያዩ ጉዳቶቹን የሚጠቁሙ ጥናቶች መውጣታቸውን ቢቀጥሉም አጠቃቀሙ ሊስተካከል አልቻለም።
በኔቸር ኮሙዩኒኬሽን ጆርናል የወጣ ጥናት እንደሚያሳየው ከ1990 እስከ 2018 ባሉት ሶስት አስርት አመታት የጣፋጭ ለስላሳ መጠጦች ፍጆታ በ16 በመቶ አድጓል።
ከሰሞኑም የአሜሪካው ተፍትስ ዩኒቨርሲቲ ይፋ ያደረገው ጥናት ስኳር ያላቸው የለስላሳ መጠጦች ፍጆታ እያደገ መሄዱን አመላክቷል።
ከ2000 እስከ 2018 ባሉት አመታት የ185 ሀገራት የለስላሳ መጠጦች ፍጆታን የዳሰሰው ጥናት በአለማችን ስኳር ያላቸው ለስላሳ መጠጦችን በመውሰድ ቀዳሚ የሆኑ 10 ሀገራትን ይፋ አድርጓል።
በዚህ ዝርዝር ውስጥ አምስት የአፍሪካ ሀገራት የተካተቱት ሲሆን፥ የላቲን አሜሪካ እና ካሪቢያን ሀገራት ስኳር ያላቸው ለስላሳ መጠጦችን በማዘውተር ተጠቃሽ ሆነዋል።
እድሜያቸው ከ20 እስከ 39 የሆኑ ወጣቶች የለስላሳ መጠጥ ፍጆታቸው በየአመቱ እየጨመረ ነው ያለው ጥናቱ፥ በታዋቂ ስፖርተኞች ጭምር የሚደረጉ የማስታወቂያ ስራዎች ለዚህ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ያብራራል።
የጥናቱ ዋና ጸሃፊ ፕሮፌሰር ዳሩይሽ ሞዛፋሪን “ወጣቶች ለምንም ነገር እንደማይበገሩ ማመናቸው ስኳር ያላቸው ለስላሳ መጠጦችን ጉዳት እንዲዘነጉት አድርጓል” ይላሉ።
ጥናቱ በሳምንት በአማካይ የሚወሰድ የለስላሳ መጠጥ ብዛትን መሰረት በማድረግ የሀገራት ደረጃን ይፋ አድርጓል።
በዚህም መሰረት፦
1. ሩዋንዳ - 34
2. ቶጎ - 29
3. ሴንት ቪንሴንት - 28
4. አልባኒያ - 23
5. ሞሪሺየስ - 21
6. ኮሎምቢያ - 20
7. ጂቡቲ - 19
8. ሴኔጋል - 18
9. ቲሞር ሌስቴ - 11
10. ባርባዶስ - 11
ጥናቱ በከተሞች እና በተማሩ ሰዎች ዘንድ የሚዘወተረውን ስኳር ያለበት ለስላሳ መጠጥ ፍጆታ ለመቀነስ እንደ ብሪታንያ ያሉ ሀገራት የጀመሩት ጥረት ሊጠናከር ይገባል ብሏል።
ለንደን የስኳር መጠን በሚያበዙ የለስላሳ መጠጥ አምራች ኩባንያዎች ላይ መጣል የጀመረችው የስኳር ግብር መጠነኛም ቢሆን ለውጥ አምጥቷል ተብሏል።
ስኳር ያላቸውን ለስላሳ መጠጦች በመጠቀም ብሪታንያ ከ185 ሀገራት 84ኛ ደረጃን ይዛለች፤ አሜሪካ እና አውስትራሊያ ደግሞ 94ኛ እና 118ኛ ላይ እንደሚገኙ ጥናቱ አመላክቷል።