ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት አደንዛዥ ዕፅ በቁጥጥር ስር ዋለ
ግምታዊ ዋጋው ከ28,386,000 ብር በላይ የሚሆን 11.4 ኪ.ግ ኮኬይን የተሰኘ አደንዛዥ ዕፅ በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡
አደንዛዥ ዕፁ የተያዘው በጉምሩክ ኢንተለጀንስ ሰራተኞች እና በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አመራሮችና ሰራተኞች አማካኝነት በቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ አለም አቀፍ መንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል መሆኑን የገቢዎች ሚንስቴር አስታውቋል፡፡
አንዲት ደቡብ አፍሪካዊት መነሻዋን ከደቡብ አፍሪካ በማድረግ 7.4 ኪ.ግ ኮኬይን ወደ ህንድ ደልሂ ስታዘዋውር የተያዘች ሲሆን የአዘር ባጃን ዜግነት ያላት ሌላ አዘዋዋሪ ደግሞ ከሞስኮ ወደ አዲስ አበባ የመጣች እና ሆቴል አርፋ ተመልሳ ወደ ባንኮክ ልትወጣ ስትል 4 ኪ.ግ ኮኬይን ይዛ በቁጥጥር ስር ውላለች።
ማንኛዉም ማህበረሰብ ከህገ ወጥ ድርጊት እራሱን በመቆጠብ ድርጊቱ ሲፈፀምም በመጠቆምና በመከላከሉ ረገድ ልክ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ተባብሮ መስራት እንደሚገባው የገቢዎች ሚንስቴር መልእክቱን አስተላልፏል፡፡
ምንጭ፡- ኢቢሲ