የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማን ህዝበ ውሳኔ የመጨረሻ ውጤት ይፋ አደረገ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ህዝበ ውሳኔን በህዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም አስፈጽሞ ህዳር 13 ቀን 2012 ዓ.ም የመጀመሪያ ደረጃ ውጤት ያሳወቀ ሲሆን የመጨረሻ ውጤቱን ደግሞ ሕዳር 24 ቀን 2012 ዓ.ም አሳውቋል፡፡
በዚህም መሰረት ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀረው የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ውጤት ሲጠቃለል የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር- 2,304,577፣ ድምጽ የሰጡ መራጮች ቁጥር-2,279,022 (98.8911 %)፣ ለሻፌታ ( ለሲዳማ ክልልነት መደራጀት ድምጽ የሰጡ) መራጮች ቁጥር -1,984,283(97%)፣ ለጎጆ (በደቡብ ክልል ለመቆየት ድምጽ የሰጡ) መራጮች ቁጥር 30,018 (1.478%)፣ዋጋ አልባ ድምጽ መስጫ ወረቀት-16,624 ሲሆን የተሰረዘ ድምጽ ቁጥር ደግሞ 248,097 ሆኗል፡፡
በአጠቃላይ ድምጽ ከተሰጠባቸው 1,692 ምርጫ ጣቢያዎች እና ተጨማሪ 169 ድምጽ መስጫ ጣቢያዎች መካከል በ233 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ቦርዱ የተለያዩ የድምርና የውጤት አለመጣጣም ችግሮች ( discrepancies) አግኝቷል፡፡ እነዚህ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ የተገኙት ችግሮች አስፈጻሚዎች ቁጥር በሚደምሩበት ወቅት የተገኘ የቁጥር ድምር ችግር እና ድምጽ የሰጡ መራጮች ድምጽ ከተመዘገቡ መራጮች ድምጽ ከፍተኛ የመሆን ችግሮች ናቸው፡፡
በመሆኑም ቦርዱ ከተመዘገበው መራጭ በላይ ድምጽ ተሰጥቶ የተገኘባቸው 127 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ያለው ውጤት እንዲሰረዝ ወስኗል፡፡ በቆጠራ እና በድምር ስሌት ስህተት ከተገኘባቸው ጣቢያዎች መካከል የታየው ልዪነት 10 ድምጽ እና ከዚያ በታች የሆኑ ልዮነቶች ዋጋ እንዳላቸው ድምጽ እንዲቆጠሩ፣ ነገር ግን ከ10 ድምጽ በላይ የድምር ልዮነት የተገኘባቸው ጣቢያዎች ውጤት እንዳይካተት ወስኗል፡፡ በዚህም መሰረት 37 ምርጫ ጣቢያዎች በከፍተኛ የድምርና የስሌት ስህተት የተነሳ ውጤታቸው ተሰርዟል፡፡
አለም አቀፍ የምርጫ ውጤት አስተዳደር ልምድን፣ የምርጫው አይነት ህዝበ ውሳኔ መሆኑን እና በተወሰኑ ጣቢያዎች የተፈጠረው አለመጣጣም በአጠቃላይ የድምጽ ሰጪዎች ድምጽ ላይ የሚያመጣውን ተጽእኖ ውስንነት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በአጠቃላይ በማጠናቀቂያ ውጤቱ 164 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ያሉ ውጤቶች እንዲሰረዙ የተደረገ ሲሆን 71 የምርጫ ጣቢያዎች ግን የድምር ልዮነቱ ከ10 ድምጽ በታች በመሆኑ ስህተት ቢኖራቸውም ውጤታቸው ዋጋ ኖሮት እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡
እንደዚህ አይነት የውጤት አለመጣጣም ከፍተኛ ውድድር ባለባቸው እንደ አገር አቀፍ ምርጫ ያሉ ውድድሮች ላይ ቢፈጠሩ የሚኖራቸውን ተጽእኖ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል በመረዳት ቦርዱ እነዚህ ችግሮች የተፈጠሩበትን ምክንያት የሚያጣራ የቴክኒክ ቡድን አቋቁሟል፡፡ የቴክኒክ ቡድኑ የማጣራት ውጤትን መሰረት አድርጎም ለቀጣዩ ምርጫ አስፈላጊውን የአቅም ግንባታ ስራዎችን፣ የአስፈጻሚዎች ስልጠና እና የምርጫ ሂደቱን የማሻሻል ስራዎችን እንደሚሰራም ቦርዱ በፌስ ቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡