ሳዑዲ ዓረቢያ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ላለው ሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ድጋፍ እንደምታደርግ ገለጸች::
የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለውን ሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለማጠናከር የሚያስችሉ ድጋፎችን ለመስጠት ያለውን ዝግጁነት አረጋገጠ።
በኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ የተመራ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በሳዑዲ ዓረቢያ ጉብኝት አድርጓል።
የልዑካን ቡድኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ እና የማሕበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ወይዘሮ ጠይባ ሃሰንን ያካተተ ሲሆን፥ ትናንት ህዳር 23 እና ዛሬ ህዳር 24/ 2012 ዓ.ም. በሪያድ የስራ ጉብኝት አድርጓል።
በጉብኝቱ የልዑካን ቡድኑ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ለሳዑዲ ዓረቢያው ልዑል አልጋ ወራሽ ሙሃመድ ቢን ሳልማን የተላከ መልዕክት ማድረሱን፣ በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አብዱላዚዝ አህመድ መናገራቸውን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘግቧል።
ልዑኩ በቆይታው ከሳዑዲ ዓረቢያ የገንዘብ ሚኒስቴርና ከሳዑዲ ዓረቢያ የልማት ፈንድ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይቷል።
በዚህ ወቅት የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለውን ሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለማጠናከር የሚያስችሉ ድጋፎችን ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጣለች፡፡
ከዚህ ባለፈም በኢትዮጵያና ሳዑዲ ዓረቢያ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግና የትብብር አድማሱን በባለብዙ ወገን መድረኮች ለማጠናከር መግባባት ላይ መደረሱንም አምባሳደር አብዱላዚዝ ገልጸዋል፡፡
ምንጭ፡- ኤፍቢሲ