የኮሎምቢያው ፕሬዝዳንት ኮኬይን "ከውስኪ የከፋ አይደለም" የሚል አከራካሪ ሃሳብ ሰነዘሩ
ፕሬዝዳንቱ አደንዛዥ እጹ እንደ አልኮል ህጋዊ ከሆነ ስርጭቱን መቆጣጠርና መግታት ይቻላልም ብለዋል

ኮሎምቢያ ቁጥር አንድ ኮኬይን አምራች እና ሻጭ ስትሆን አሜሪካ ቀዳሚዋ የአደንዛዥ እጹ መዳረሻ ናት
የኮሎምቢያው ፕሬዝዳንት መንግስታቸው ስርጭቱን መቆጣጠር ያልቻለውን ኮኬይን "ከውስኪ የከፋ አይደለም" የሚል አስተያየት መስጠታቸው አነጋጋሪ ሆኗል።
ፕሬዝዳንቱ ከሰሞኑ በቴሌቪቭን በተላለፈ የሚኒስትሮች ስብሰባ "ኮኬይን ህገወጥ የሆነው በላቲን አሜሪካ ስለሚመረት እንጂ ከውስኪ የከፋ ጉዳት ኖሮት አይደለም" ብለዋል።
በየትኛው የምርምር ጽሁፍ ላይ እንደወጣ ሳይጠቅሱም "ተመራማሪዎች ይህንኑ (ከውስኪ እንደማይከፋ) አረጋግጠዋል" ነው ያሉት።
ፕሬዝዳንት ጉስታቮ ፔድሮ አለማቀፉን የኮኬይን ኢንዱስትሪ በቀላሉ ለማፈራረስ አደንዛዥ እጹ ህጋዊ እንዲሆንም ጠይቀዋል።
"ሰላም ከፈለጋችሁ፤ የአደንዛዥ እጽ ንግድ መረብን መበጣጠስ ካሻችሁ ኮኬይን በአለማቀፍ ደረጃ ህጋዊ መሆን አለበት፤ ከዚያ ልክ እንደ ወይን ይሸጣል" ሲሉም ተደምጠዋል።
ፕሬዝዳንት ፔትሮ "ፌንታይል" የተሰኘው አደንዛዥ እጽ ግን "አሜሪካውያንን እየገደለ የሚገኝ ነው፤ ከኮሎምቢያ የሚሰራ አይደለም" ብለዋል።
ግራ ዘመሙ መሪ በ2022 ስልጣን ከያዙ ጀምሮ በአደንዛዥ እጽ ዝውውር ላይ ጠንካራ ዘመቻ እንደሚከፍቱ ቢገልጹም የኮኬይን ምርት እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አልሄደም ይላል የሲኤንኤን ዘገባ።
በ2023 ከ253 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኮካ ቅጠል ተሸፍኖ ከ2 ሺህ 600 ሜትሪክ ቶን በላይ ኮኬይን ተመርቷል፤ ይህም ከ2022ቱ በ53 መጨመሩን ዘገባው ያክላል።
የአለማችን ቀዳሚዋ ኮኬይን አምራች እና ለውጭ ገበያ አቅራቢ ሀገር የኮኬይን ንግድን ህገወጥ ነው ብትልም በ2022 ብቻ ከእጹ የወጪ ንግድ 18 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ማግኘቷን ብሉምበርግ ያወጣው መረጃ ያመላክታል።
የኮሎምቢያ ኮኬይን ቀዳሚ መዳረሻ የሆነችው አሜሪካ የደቡብ አሜሪካዋን ሀገር የኔቶ አባል ያልሆነች ዋነኛ አጋር አድርጋ በተለይ በአደንዛዥ የእጽ ዝውውር በትብብር ትሰራለች።
ይሁን እንጂ በበርካታ ሀገራት ህገወጥ የሆነውን አደንዛዥ እጽ ዝውውር መግታት ላይ የሚጠበቀውን ውጤት እንዳላመጡ የሀገራቱ መሪዎች ያምናሉ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኮኬይን በአለማችን በብዛት ጥቅም ላይ ከሚውሉ አደንዛዥ እጾች አራተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና በርካታ የጤና እክሎችን እንደሚያስከትል ይገልጻል። ኮኬይን ረፍት የለሽ ህመም ላለባቸው ሰዎች በመድሀኒት መልኩ በሀኪሞች አማካኝነት እንደሚሰጥ ይታወቃል።