ድሮኖቹ ከሞሮኮ ኮኬይን አደንዛዥ እጽን ጭነው ነበር ተብሏል
ስፔን የአደንዛዥ እጽ ማዘዋወሪያ ሶስት ሰው አልባ ባህር ሰርጓጅ ድሮኖችን በቁጥጥር ስር ማዋሏን አስታወቀች፡፡
ድሮኖቹ ኮኬይን የተባለውን አደንዛዥ እጽ ከሞሮኮ ጭነው ወደ ስፔን ሊገቡ ሲሉ መያዛቸውም ነው የተነገረው፡፡
ዝውውሩን መግታቱን የገለጸው የሃገሪቱ ፖሊስ ከህገ ወጥ ዝውውሩ ጋር በተያያዘ 8 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል፡፡
ወደ ፈረንሳይ ሊዘዋወር ነበር የተባለለትን ኮኬይን የጫኑት ድሮኖቹ እያንዳንዳቸው 200 ኪሎ ግራም ያል የመጫን አቅም እንዳላቸው ተነግሯል፡፡ ሆኖም ምን ያህል ኪሎ ግራም ኮኬይንን ጭነው እንደተያዙ አልተገለጸም፡፡
በእንዲህ ዐይነት መንገድ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ሲገጥሙት ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ያስታወቀው ፖሊስ ሁኔታው ወንጀለኞች በጅብራልታል መተላለፊያ በኩል በርከት ያሉ ህገ ወጥ ዝውውሮችን ለማድረግ እንደሚያስችላቸው ገልጿል፡፡
በጅብራልታል መተላለፊያ በኩል ከሞሮኮ ስፔን ለመግባት 15 ኪሎ ሜትሮችን በሜዲትራኒያን ባህር ላይ መጓዝን ብቻ ነው የሚጠይቀው፡፡
ይህም ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ሰው አልባ ቴክኖሎጂዎችን እየተጠቀሙ በቀላሉ በስፔን፣ በፈረንሳይ፣ በጣሊያን እና በሌሎችም የአካባቢው ሃገራት እንደልብ ለመንቀሳቀስ አስችሏቸዋል፡፡