የ9 ዓመቱ ታዳጊ ይህንን አደገኛ የሆነ አደንዛዥ እፅ ሊያዘዋውር የቻለው ተገዶ ሊሆን ይችላል ተብሏል
የብሪታኒያ ፖሊስ በእድሜ ትንሹ ነው የተባለ የአደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪ በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።
ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋለው የአደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪ የ9 ዓመት እድሜ ያለው መሆኑም ታውቋል።
የብሪታኒያ ጋዜጣ የሆነው ‘ሚረር’ እንዳስነበበው በአደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪነት ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለው ታዳጊ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነው።
ታዳጊው ሊያዘዋውረው እና ሊያከፋፍለው የነበረ ‘ናርኮቲክ’ የተባለ አደገኛ አደንዛዥ እፅ በእጁ መገኘቱንም ነው ፖሊስ ያስታወቀው።
በእንግሊዝም ሆነ በዌልስ አንድ ሰው ጥፋተኛ ተብሎ ፍርድ ቤት ተከሶ ሊቆም የሚችለው እድሜው 10 ዓመት እና ከዚያ በላይ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም ታዳጊው ክስ ተመስርቶበት ፍርድ ቤት ላይቆም ይችላልም ብሏል ጋዜጣው።
ጉዳዩን የያዙት ባለስልጣናት በእድሜ ትንሹን የአደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪ ማንነት ከመግለጽ መቆጠባቸውም ነው የተነገረው።
በርካታ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ግን የ9 ዓመቱ ታዳጊ ይህንን አደገኛ የሆነ አደንዛዥ እፅ ሊያዘዋውር የቻለው ተገዶ ሊሆን ይችላል ያሉ ሲሆን፤ ከእጹ ጀርባም ግዙፍ አደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪ ቡድን ሊኖር ይችላል የሚል መላ ምት አስቀምጠዋል።