“ትረፊ ያላት ነፍስ” ከጎፋ የመሬት ናዳ በተዓመር የተረፉት ረ/ኢንስፔክተር በዛብህ ቡናሮ
ረ/ኢንስፔክተር በዛብህ እርዳታ በመስጠት ላይ በደረሠው ናዳ ሙሉ በሙሉ በጭቃ ከተዋጡ በኋላ በህይወት ወጥተዋል
ረ/ኢንስፔክተር በዛብህ “ እኔ ከዚህ የተፈረፍኩት የተለየ ብርታት ኖሮኝ አይደለም፤ እግዚአብሄር ነው እጄን ይዞ ያወጣኝ” ብለዋል
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን በገዜ ጎፋ ወረዳ በኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ትናንት ጠዋት በደረሰ የመሬት ናዳ አደጋ የበርካችን ህይወት መቅጠፉ ይታወቃል።
አደጋው መጀመሪያ ሶስት ቤተሰብ ላይ የደረሰ ሲሆን፤ ይህንን ሰምተው እነሱን ለማዳን ርብርብ በሚደረግት ወቅት ድጋሚ ባጠመ የናዳ አደጋ የበርካቶች ህይወት ማለፉን ተነግሯል።
በአደጋው ሰለባ ከሆኑት ሰዎች መካከል የወረዳው ፖሊስ አባላትን የሚገኙበት ሲሆን፤ የገዜ ጎፋ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ረ/ኢንስፔክተር በዛብህ አደጋው በደረሰበት ቦታ ላይ የነበሩ እና በተዓመር ህይወታቸው ከተረፈ የፖሊስ አመራች መካከል አነዱ ናቸው።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባጋራው መረጃ የገዜ ጎፋ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ረ/ኢንስፔክተር በዛብህ ቡናሮ ጉዳይ “አትጥፊ ያላት ነብስ ፖሊስ ለህዝብ” በሚል አጋርቷል።
ኮሚሽኑ “ረ/ኢንስፔክተር በዛብህ ቡናሮ አባሎችን ይዞ ወደ አደጋው ስፍራ ገብቶ እርዳታ እየሠጠ ባለበት ወቅት ድንገት የደረሠው ናዳ ሙሉ በሙሉ ሰውነቱን እንደቀበረው እና የአከባቢው ሰዎች ገመድ ወርውረው እንዲይዝ አድርገው ተጎትቶ ህይዎቱ ተርፏል” ብሏል።
የገዜ ጎፋ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ረ/ኢንስፔክተር በዛብህ ስለ ለአካባው መገናኛ ብዙሃን ሁኔታው ሲያስታውስም፤ የመጀመሪያ አደጋ በደረሰ ማግስት ከወረዳው እተዳዳሪ በደረሳቸው ጥቆማ መሰረት አባላቶቻውን ይዘው ወደ ስፍራው በማቅናት የነፍስ አድን ስራ ላይ መሰማራታቸውን ይናገራሉ።
ረ/ኢንስፔክተር በዛብህ፤ አደጋው እሁድ ምሽት ላይ መድረሱን በማስታወስ፤ “ንጋት 11 ሰዓት ላየ የወረዳው አስተዳዳሪ ደውሎልኝ የቀበሌ አስተዳዳሪው እና ሙሉ ቤተሰቦቻቸው በናዳ አደጋ ሞተዋል በሚል ነገረኝ” ይላሉ።
“የፖሊስ አባላቶችን ይዤ ቦታው ላይ ደረስኩኝ” ያሉት ረ/ኢንስፔክተር በዛብህ፤ “ናዳው ወደ ደረሰበት ቦታ በእግራችን ገባን፤ ሰዎች ወደ ስፍራው እንዳይገቡ ስንከልከል ነበር፤ ነገር ግን የሞተው የቀበሌው አስተዳዳሪ ስለነበረ በርካቶች እያለቀስ ተከትለውን ወደ ስፍራው ገቡ” ብለዋል።
“ሰዎቹን ተመለሱ ብለን እየተቆጣን እያለ ከላይ ከፍተኛ የሆነ የፍንዳታ ድምጽ ተሰማ” ያሉት ረ/ኢንስፔክተር በዛብህ፤ “መጀመሪያ ድንጋይ ተወርውሮ መጣ፤ ሁላችንም እግራችን ወዳመራን መሮጥ ጀመርን፤ ከላይ የመጣው ናዳም ጠልፎ ጣለኝ” ሲሉም ክስተቱን ያስታውሳሉ።
“የመጣው ሁለተኛው ናዳ ፖሊሶችን ጨምሮ ተመለሱ እያለን ተከትለውን ለነብስ አድን ስራ የገቡትን 300 ገደማ ሰዎች እዛው ጸጥ አደረገ” ብለዋል ረ/ኢንስፔክተር በዛብህ።
ረ/ኢንስፔክተር በዛብህ “ እኔ ከዚህ የተፈረፍኩት የተለየ ብርታት ኖሮኝ አይደለም፤ ሮጬ አምልጫለሁም አልልም፤ እግዚአብሄር ነው እጄን ይዞ አውጥቶ ጣለኝ” ሲሉም በተዓምር ስለመትረፋቸው ይናገራሉ።
“የስራ ባልደረቦቼን ይዤ መጥቼ አስከሬን ነው ይዤ የተመለስኩት” የሚሉት ረ/ኢንስፔክተር በዛብህ፤ እኔ የተረፍኩት በእግዚአብሄር እጅ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን በገዜ ጎፋ ወረዳ በኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ባሰለፍነው ሰኞ ጠዋት በደረሰ የመሬት ናዳ አደጋ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 257 መድረሱን የተመድ እርዳታ ማስተባበርያ ቢሮ (ኦቻ ) አስታውቋል።
በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር እስከ 500 ሊደርስ እንደሚችል ኦቻ ዛሬ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።