ኮሎምቢያ ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን አቋረጠች
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጉስታቮ ፔትሮ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጋዛ “የዘር ፍጅት” እየፈጸሙ ነው ሲሉ ከሰዋል

እስራኤል የኮሎምቢያውን ፕሬዝዳንት “ጸረ ሴማዊ እና በጥላቻ የተሞሉ” ናቸው በሚል ውሳኔያቸውን አውግዛለች
ኮሎምቢያ ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን አቋረጠች።
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጉስታቮ ፔትሮ ትናንት የአለም የሰራተኞች ቀን በቦጎታ ሲከበር “ከሀሙስ (ዛሬ) ጀምሮ ከእስራኤል ጋር ግንኙነታችን እናቋርጣለን” ያሉ ሲሆን፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁንም በ”ዘር ጭፍጨፋ” ከሰዋል።
ፕሬዝዳንቱ የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ በኔታንያሁ ላይ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ የቆዩ ሲሆን፥ ሀገራቸው ደቡብ አፍሪካ በአለማቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት በእስራኤል ላይ ያቀረበችውን የዘር ፍጅት ክስ ለመቀላቀልና ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗን ማሳወቃቸውን ሬውተርስ አስታውሷል።
“ፍልስጤማውያን ካለቁ ሰብአዊነትም ይሞታል” ያሉት ፕሬዝዳንት ፔትሮ፥ ሀገራት በጋዛ እየተከናወነ ያለውን ነገር ሁሉ አይተው እንዳላዩ መሆኑ የለባቸውም፤ ሳይረፍድ መድረስ አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ግን ፕሬዝዳንቱን “ጸረ ሴማዊ እና በጥላቻ የተሞሉ” ናቸው በሚል ውሳኔያቸውን አውግዘዋል።
“ጉስታቮ ፔትሮ ህጻናትን ላቃጠለው፣ ሴቶችን ለደፈረውና ንጹሃንን አፍኖ ከወሰደው ሃማስ ጎን በመሰለፋቸው ታሪክ ሁሌም በክፉ ያስታውሳቸዋል”ም ነው ያሉት።
ሃማስ በበኩሉ የኮሎምቢያ ውሳኔ “ለነጻነታቸው መስዋዕትነት እየከፈሉ ለሚገኙ ፍልስጤማውያን ትልቅ ድል ነው” በሚል ፕሬዝዳንት ፔትሮን አመስግኗል።
ቡድኑ ባወጣው መግለጫ ሌሎች የላቲን አሜሪካ ሀገራትም የቦጎታን አርአየነት በመከተል ከእስራኤል ጋር ግንኙነታቸውን እንዲያቋርጡ ጠይቋል።
ኮሎምቢያ ከእስራኤል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ያቋረጡትን ቦሊቪያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ቤሊዝ ተቀላቅላለች።
ቦሊቪያ ባለፈው የፈረንጆቹ አመት ህዳር ወር ላይ ከቴል አቪቭ ጋር ግንኙነቷን ስታቋርጥ፥ ኮሎምቢያ፣ ቺሊ እና ሆንዱራንስ አምባሳደሮቻቸውን መጥራታቸው ይታወሳል።