የደቡብ አፍሪካ ፓርላማ ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማቋረጥ ወሰነ
ምክርቤቱ በፕሪቶሪያ የሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ እንዲዘጋም በአብላጫ ድምጽ ውስኗል
ከውሳኔው በፊት አምባሳደሯን የጠራችው እስራኤል ስለምትወስደው እርምጃ አልገለጸችም
የደቡብ አፍሪካ ፓርላማ ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማቋረጥ ወስኗል።
የምክርቤቱ አባላት በ249 ድጋፍና በ91 ተቃውሞ በፕሪቶሪያ የሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ እንዲዘጋም ነው የወሰኑት።
እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ የምትወስደውን እርምጃ አጥብቀው ሲቃወሙ የቆዩት ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ የፓርላማውን ውሳኔ ተፈጻሚ ያደርጉታል ወይ የሚለው ተጠባቂ ነው።
በተቃዋሚው ኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ ፓርቲ የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ በገዥው አፍሪካ ናሽናል ኮንግረንስ (ኤኤንሲ) ድጋፍ ተችሮታል።
የውሳኔ ሃሳቡ እስራኤል በጋዛ ተኩስ ካላቆመችና ዘላቂ ሰላምን የሚያመጣና በመንግስታቱ ድርጅት አደራዳሪነት የሚደረስ ስምምነት ላይ ካልደረሰች ደቡብ አፍሪካ ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ታቋርጣለች ይላል።
እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን እንዳሳለፉት የአፓርታይድ አገዛዝ የምትመለከተው የኔልሴን ማንዴላ ሀገር ለፍልስጤም ነጻ ሀገርነት እውቅና ትሰጣለች።
የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረንስም ከፈረንጆቹ 1994 ጀምሮ በፍልስጤም ጉዳይ የማይለዋወጥ አቋም መያዙን ሲገልጽ መቆየቱንም ነው ሬውተርስ የዘገበው።
እስራኤል ከጥቅምት 7ቱ የሃማስ ጥቃት በኋላ እየወሰደች ያለውን ድብደባም በጽኑ በመቃወም የአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የጦር ወንጀል መፈጸሙን እንዲያጣራ መጠያቋ ይታወሳል።
እስራኤል የደቡብ አፍሪካ አፍሪካ ፓርላማ ግንኙነት የማቋረጥ የውሳኔ ሃሳቡ ላይ ድምጽ ከመስጠቱ በፊት አምባሳደሯን ወደ ቴል አቪቭ መጥራቷ ይታወሳል።
ቴል አቪቭ በቀጣይ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ስለሚኖራት ግንኙነት እስካሁን የሰጠችው መግለጫ የለም።