ስፔን ለፍልስጤም ሀገርነት እውቅና ልትሰጥ ነው
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ሌሎች የአውሮፓ ሀገራትም የማድሪድን እርምጃ እንዲከተሉ ጠይቀዋል
ከ193 የመንግስታቱ ድርጅት አባል ሀገራት 139ኙ ለፍልስጤም ሀገርነት እውቅና ሰጥተዋል
ስፔን ለፍልስጤም ነጻ ሀገርነት እውቅና ለመስጠት መዘጋጀቷን አስታወቀች።
ማድሪድ እውቅናውን የምትሰጠው በመጪው ሀምሌ ወር መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ገልጸዋል።
የመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝታቸውን በዮርዳኖስ የጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በኳታር እና ሳኡዲ አረቢያ በሚኖራቸው ቆይታ በጋዛው ጦርነት ዙሪያ ይመክራሉ መባሉን የስፔን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ከ27ቱ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ውስጥ ለፍልስጤም ነጻ ሀገርነት እውቅና የሰጡት ዘጠኙ ብቻ ናቸው።
የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ በአማን ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃለምልልስ፥ በርካታ የህብረቱ አባል ሀገራት ለፍልስጤም እውቅና እንዲሰጡ ግፊት እየተደረገ ነው ብለዋል።
አየርላንድ፣ ማልታ እና ስሎቫኒያም እስራኤል በሃይል የያዘችው ዌስትባንክ እና የጋዛ ሰርጥ የፍልስጤም ሉአላዊ ግዛት መሆኑን በመቀበል እውቅና ለመስጠት መስማማታቸውን ሳንቼዝ ይፋ አድርገዋል።
እስራኤል የአራቱ ሀገራት ለፍልስጤም እውቅና የመስጠት እቅድ “ለሽብርተኝነት የሚቀርብ ሽልማት” አድርጋ እንደምትመለከተውና የጋዛውን ጦርነት በንግግር ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት የሚያውክ ነው በሚል ተቃውሞዋን ማሰማቷን ሬውተርስ ዘግቧል።
የአረብ ሀገራትና የአውሮፓ ህብረት የእስራኤልና ፍልስጤም ጦርነትን ለመቋጨት ይረዳል በተባለ “የሁለት መንግስት መፍትሄ” ዙሪያ በህዳር ወር 2024 በስፔን ምክክር ለማድረግ ተስማምተዋል።
ከፈረንጆቹ 1988 ጀምሮ ከ193 የመንግስታቱ ድርጅት አባል ሀገራት 139ኙ ለፍልስጤም ሀገርነት እውቅና ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ለፍልስጤም የሀገርነት እውቅና ቢሰጡም፥ ምዕራባውያን ነጻዋ ፍልስጤም የምትፈጠረው ከእስራኤል ጋር በሚደረግ ስምምነት ነው በሚል እውቅና ነፍገዋታል።
እስራኤል በጋዛው ጦርነት እየፈጸመችው ያለው ድብደባ ግን የተለያዩ ሀገራትን አቋም እያስለወጠ ይገኛል።
ፈረንሳይም በቅርቡ ለፍልስጤም እውቅና መስጠት እንደ ነውር የሚቆጠርበት ጊዜ አብቅቷል ማለቷ የሚታወስ ነው።