የኮሎራዶ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ትራምፕ በቀጣዩ ምርጫ እንዳይፎካከሩ ወሰነ
ፍርድ ቤቱ የቀድሞው ፕሬዝዳንት በ2021ዱ የካፒቶል ሂል ሁከት የነበራቸው ተሳትፎ ህገመንግስታዊ ጥሰት አለው በሚል ነው ውሳኔውን ያሳለፈው
የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ውሳኔውን በመቃወም ይግባኝ እጠይቃለሁ ብሏል
የኮሎራዶ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ትራምፕ በቀጣዩ አመት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በኮሎራዶ ግዛት እንዳይፎካከሩ ውሳኔ አሳለፈ።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ከሶስት አመት በፊት በካፒቶል ሂል በተፈጠረው ሁከት ተሳትፎ አድርገዋል፤ ይህም ህገመንግስቱን ይቃረናል በሚል ነው ፍርድቤቱ ውሳኔውን ያሳለፈው።
በአሜሪካ ህገመንግስት 14ኛ ማሻሻያ አንቀጽ 3 ላይ የሰፈረው መንግስትን በሃይል ለመጣል ሁከት የመቀስቀስ ወንጀል ተጠቅሶ እጩ ፕሬዝዳንታዊ ተፎካካሪ ሲታገድ ይህ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።
ፍርድቤቱ አመጽ በመቀስቀስና በመምራት ትራምፕ ላይ ውሳኔ ያሳለፈበት አንቀጽ በቀጥታ ፕሬዝዳንቶችን ተጠያቂ አያደርግም፤ የመናገር ነጻነታቸውም አልተከበረም የሚለው ክርክር ቀጥሏል።
ውሳኔው ከኮሎራዶ ግዛት ውጭ በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው መፎካከራቸውን የሚከለክል ባይሆንም ከምርጫው በፊት ክስ ለበዛባቸው ትራምፕ መልካም ዜና አይደለም።
የኮሎራዶ ግዛት የምርጫ አስፈጻሚዎች ትራምፕ በቀጣዩ ምርጫ የመሳተፋቸው ጉዳይ እስከ ጥር 5 2023 ሊለይለት ይገባል ብለዋል።
የኮሎራዶው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ “የተፈበረከ ቅጥፈት” ነው ያለው የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ፥ ለአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድቤት ይግባኝ እንደሚጠይቅ መግለጹን ሬውተርስ ዘግቧል።
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔውን ካጸናው ትራምፕ በ2024ቱ ምርጫ በኮሎራዶ አይሳተፉም።
ይሁን እንጂ የኮሎራዶው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ሊሻር እንደሚችል ይገመታል።
በኒው ሃምፕሻየር፣ ሚኒሶታ እና ሚቺጋን በተመሳሳይ ፕሬዝዳንቱን ከምርጫው ለማስወጣት የተደረጉ ሙከራዎች ሳይሳኩ መቅረታቸው የሚታወስ ነው።
ዶናልድ ትራምፕና ደጋፊዎቻቸው እየቀረቡ የሚገኙት ክሶች ዴሞክራቶች የሚያቀነባብሯቸውና ፖለቲካዊ ጣልቃገብነት የሚታይባቸው እንደሆኑ ያምናሉ።
የአሜሪካ ህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አፈ ጉባኤው ማይክ ጆንሰንም፥ የኮሎራዶ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔን በሪፐብሊካን ፓርቲ ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው ብለውታል።
“ማንኛውም ድምጽ ለመስጠት የተመዘገበ ሰው የፈቀደውን እንዲመርጥ ሊከለከል አይገባውም” ሲሉም ነው የተናገሩት።
ትናንት በአይዋ ግዛት የምርጫ ቅስቀሳ ላይ የነበሩት ትራምፕ እስካሁን በቀጥታ ስለውሳኔው መግለጫ ባያወጡም፥ የገቢ አሰባሳቢ ተቋማቸው ለደጋፊዎቻቸው በላከው የኢሜል መልዕክት “እንዲህ ነው አምባገነንነት የሚወለደው” ሲል ተቃውሞውን አሰምቷል።