ዶናልድ ትራምፕ በተመሰረተባቸው ክስ መሰረት በጆርጂያ እስር ቤት እጅ በሰጡ በ20 ደቂቃ ከእስር ተፈተዋል
ዶናልድ ትራምፕ በ200 ሺህ ዶላር ዋስ ከእስር ተፈቱ።
የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር የሆነችው አሜሪካንን ከፈረንጆቹ 2016 እስከ 2020 ድረስ በፕሬዝዳንትነት የመሩት ዶናልድ ትራምፕ የተለያዩ ክሶች ተመስርቶባቸዋል፡፡
ከ2020 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እና አስገድዶ ደፈራ ጋር ጋር በተያያዘ 91 ክስ የቀረበባቸው ዶናልድ ትራምፕ ሁሉንም ክሶች እንዳልፈጸሙ ተናግረዋል፡፡
እንደ ዶናልድ ትራምፕ ገለጻ ይህ ሁሉ ክስ የቀረበባቸው በስልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሚቀጥለው ዓመት በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዳይፎካከሯቸው በማሰብ ነው፡፡
ከሶስት ዓመት በፊት በተካሄደው የ2020 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በጆርጂያ ግዛት የመራጮችን ድምጽ ለማስቀየር ተደራድረዋል በሚል ክስ የቀረበባቸው ትራምፕ ክሱን ውድቅ አድርገዋል፡፡
"እኔ ምንም የፈጸምኩት ጥፋት የለም፣ ንጹህነቴን ሁሉም ያውቃል እነሱ በምርጫ ላይ ጣልቃ ገብተኃል ይላሉ" ሲሉ ለብዙሃን መገናኛዎች ተናግረዋል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በተመሰረተባቸው ክስ መሰረት በጆርጂያ እስር ቤት እጅ የሰጡ ሲሆን ከታሰሩ 20 ደቂቃ በኋላ በዋስ ከእስር ተፈተዋል፡፡
200 ሺህ ዶላር የዋስ ከፍለው ከእስር የተለቀቁት የቀድሞው ፕሬዝዳንት በሚቀጥለው ዓመት በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ክርክር ላይ ሳይገኙ ቀርተዋል፡፡
በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ታሪክ ክስ የተመሰረተባቸው እና የታሰሩ በመባል የመጀመሪያው ሰው እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡
በ2024 በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እየተፎካከሩ ካሉ እጩ ፕሬዝዳንቶች መካከል ዶናልድ ትራምፕ በህዝብ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው እጩ ሆነዋል፡፡
የ77 ዓመቱ ዶናልድ ትራምፕ በጆርጂያ ከምርጫ ጋር በተያያዘ የተመሰረተባቸው ክስ ከሁለት ወር በኋላ መታየት ይጀምራል ተብሏል፡፡