በድጋሚ ፕሬዝደንት ከሆንኩ "ከአንድ ቀን በስተቀር" አምባገነን አልሆንም- ትራምፕ
ከፈረንጆቹ 2017 እስከ 2021 ድረስ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነው ያገለገሉት ትራምፕ፣በባይደን መሸነፋቸውን አልተቀበሉም
በቴሌቪዥን በተላለፈ የአዳራሽ ፕሮግራም ላይ በድጋሚ ቢመረጡ ተቀናቃኞቻቸውን ይበቀሉ እንደሆነ የተጠየቁት ትራምፕ አልበቀልም ብለዋል
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በድጋሚ ፕሬዝደንት ሆነው የሚመረጡ ከሆነ "ከአንድ ቀን በስተቀር" አምባገነን እንደማይሆኑ ተናገሩ።
ዶናልድ ትራምፕ ይህን ያሉት ዲሞክራቶች እና የተወሰኑ ሪፐብሊካኖች የ2024ቱን ምርጫ ትራምፕ የሚያሸንፉ ከሆነ አሜሪካ በአምባገነን ጥላ ስር ትወድቃለች የሚል ማስጠንቀቂያ ማሰማታቸውን ተከትሎ ነው።
በቴሌቪዥን በተላለፈ የአዳራሽ ፕሮግራም ላይ በድጋሚ ቢመረጡ ተቀናቃኞቻቸውን ይበቀሉ እንደሆነ የተጠየቁት ትራምፕ አልበቀልም ብለዋል።
ትራምፕ ስልጣን ከያዙ በኋላ አምባገነን ይሆኑ እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ "አይ አይ፣ ከአንድ ቀን በስተቀር" አልሆንም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ትራምፕ "አንድ ቀን" ያሉት ፕሬዝደንታዊ ስልጣናቸውን ተጠቅመው ከሜክሲኮ ጋር የሚያገናኘውን የደቡብ ድንበር እንደሚዘጉ ለማመላከት ነው።
በድጋሚ መመረጥ የሚፈልጉት ትራምፕ የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን እንደሚበቀሉ ሲገልጹ ቆይተዋል።
ትራምፕ በዚህ አመት ባደረጓቸው የምርጫ ቅስቀሳዎች ላይ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን፣ በርካታ ክስ ያቀረቡባቸው አቃቤ ህጎች እና የፍትህ ዲፖርትመንት ሊበቀሏቸው ከሚችሏቸው አካላት ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከፈረንጆቹ 2017 እስከ 2021 ድረስ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነው ያገለገሉት ትራምፕ፣በባይደን መሸነፋቸውን አልተቀበሉም።
በዚህ ምክንያት ትራምፕ ምርጫው እንደተጭበረበረ በመግለጽ በ2021 በካቲቶል ሂል ተቃውሞ እንዲቀሰቀስ አድርገዋል ተብለው ይከሰሳሉ።
ትራምፕ የአሜሪካን ዲሞክራሲ እና ብሔራዊ ሚስጥርን አደጋ ላይ በመጣል ተከሰው ፍርድ ቤት እየተመላሱ ነው።