የቀድሞው የጋምቢያ ፕሬዝዳንት ጃሜህ በግድያና አስገድድ መድፈር ወንጆለኞች ተጠያቂ ናቸው ተባለ
የጋምቢያ እውነት እና እርቅ ኮሚሽን “ጃሜህ በ22 ዓመታት የስልጣን ዘመናቸው 44 ከባባድ ወንጀሎች ፈጽሟል” ብሏል
ጃሜህ በፈረንጆቹ 2016 በተካሄደው ምርጫ ሽንፈትን አልቀበልም ብለው ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ መኮብለላቸው ይታወሳል
የጋምቢያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጃሜህ ለ22 ዓመታት በዘለቀው የስልጣን ቆይታቸው በሀገሪቱ ለተፈጸሙት ግድያዎች፣ሰቆቃዎቸ እና የአስገድዶ መድፈር ወነጀሎች ተጠያቂ መሆናቸውን የጋምቢያ እውነት እና እርቅ ኮሚሽን ገልጿል፡፡
በፈረንጆቹ 2016 በተካሄደው ምርጫ ሽንፈትን ለመቀበል ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ጃሜህ ጋምቢያን ለቀው ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ መሰደዳቸውን ተከትሎ የተቋቋመው ኮሚሽን ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመላክተው ከሆነ፤ ፕሬዝዳንቱ በስልጣን ዘመናቸው ለተፈጸሙ ወንጀሎች ተጠያቂ የሚያደርጉ በርካታ ምርመራዎች ማካሄዱን አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ምስክርነት መሰረት በማድረግ፤በጃሜህ ዘመን የተፈፀሙ የመብት ጥሰቶችን በማስመልከት ላለፉት ሶስት አመታት ሲያደርገው የቆየውን ምርመራ ለፕሬዚዳንት አዳማ ባሮው በዚህ ወር መጀመሪያ ሪፖርት ቢያደርግም ለህዝብ ይፋ የሆነው በትናትናው እለት ነው፡፡
ኮሚሽኑ ለጥቃቱ ተጠያቂ የሆኑ አካላት በህግ እንዲጠየቁም ምክረ-ሃሳብ አቅርቧል፡፡
ኮሚሽኑ ያቀረበውን ሪፖርት በተመለከተ ጃሜህም ሆነ ቃል አቀባያቸው አስተያየት እንዲሰጡበት ጥረት ቢደረግም ማግኘት አለማቻሉን ሮይተረስ ዘግቧል።
“እንደፈረንጆቹ በ1994 መፈንቅለ መንግስት ወደ ስልጣን የመጡት ጃሜህ እና ጀንግልስ በመባል የሚታወቁትን ግላዊ ቡድንናቸውን ጨምሮ በጋዜጠኞች ፣በቀድሞ ወታደሮች ፣በፖለቲካ ተቃዋሚዎች እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ ለተፈጸሙ 44 ወንጀሎች ተጠያቂ ናቸው”ም ብሏል ኮሚሽኑ።
ኮሚሽኑ በ2004 የተፈጸመው የጋዜጠኛ ዴይዳ ሃይዳራ ግድያ፣ በ2000 የተገደሉት ሰባት ሲቪሎች፣ በ2005 የተገደሉት 59 የምዕራብ አፍሪካ ስደተኞች እና በሶስት ሴቶች ላይ የተፈጸመው የአስገድዶ መድፈር ወይም ፆታዊ ጥቃት የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጃሜህ እና ቡዱናቸው ከፈጸሟቸውና ከሚጠየቁባቸው ወንጀሎች እንደሆኑም በአብነት አንስቷል፡፡
ኮሚሽኑ በሪፖርቱ "የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር በያህያ ጃሜህ እና ተባባሪዎቻቸውን በአለምአቀፍ ፍርድ ቤት ክስ ልትመሰርት ይገባል" የሚል ምክረ-ሃሳብም አቅርቧል።