በጋምቢያውያን በትናትናው እለት ፕሬዝዳንታቸውን ለመምረጥ ድምጽ ሲሰጡ ውለዋል
በጋምቢያ በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ፕሬዝዳንት አዳማ ባሮው በጠባብ ውጤት እየመሩ መሆኑ ተነግሯል።
በጋምቢያውያን በትናትናው እለት ፕሬዝዳንታቸውን ለመምረጥ ድምጽ ሲሰጡ መዋላቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ዛሬ ጠዋት ላይ የ17 ምርጫ ክልሎችን ውጤት ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ ፕሬዚዳንት አዳማ ባሮው በ17 ምርጫ ክልሎች ላይ በተደረገው ቆጠራ ከግማሽ በላይ ድምፅ አግኝተዋል ነው የተባለው።
ፕሬዝዳንት አዳማ ባሮው በምርጫው በማሸነፍ ሀገሪቱን ለመምራት ከተፎካካሪያቸው በበለጠ ተጨማሪ ድምጽ እንደሚያስፈልጋቸውም ነው የተነገረው።
በሀገሪቱ በአጠቃላይ 53 የምርጫ ክልሎች ያሉ ሲሆን፤ በርካታ ሰዎች ድምጽ የሰጡበት የምርጫ ጣቢያዎች ቆጠራ ላይ በመሆናቸው እስካሁን ውጤት አልተገለፀም።
የሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ውጤት ተጠናቆ ይፋ በሚደረግበት ጊዜ አሁን ይፋ የተደረገው ውጤት ላይ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ይጠበቃል።
በሀገሪቱ ከ27 ዓመት ወዲህ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ያያህ ጃሜህ ያልተሳተፉበት የመጀመሪያውን ምርጫ ነው በትናትናው እለት ያካሄደችው።
ፕሬዝዳንት ያያህ ጃሜህ በ2016 በሀገሪቱ በተደረገው ምርጫ መሸነፋቸውን ተከትሎ ስልጣን አላስረክብም ካሉ በኋላ በተፈጠረ ግጭት ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ መኮብለላቸው ይታወሳል።
በምእራብ አፍሪካ የምትገኘው ጋምቢያ አጠቃላይ የህዝብ ብዛቷ 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ነው፤ ቱሪዝም ከፍተኛ የገቢ ምንጯ ሲሆን፤ የለውዝ እና የአሳ ምርት ወደ ውጭ በመላክ ትታወቃለች።