ጭፍጨፋውን የፈጸሙት ቡድኖች “አማሮችና ወልቃይቴዎች“ ያሏቸውን ከቤት ቤት እየዞሩ ነው የገደሉት ተብሏል፡፡
ጭፍጨፋውን የፈጸሙት ቡድኖች “አማሮችና ወልቃይቴዎች“ ያሏቸውን ከቤት ቤት እየዞሩ ነው የገደሉት ተብሏል፡፡
ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በማይካድራ ከተማ የተፈጸመው የዜጎች ጭፍጨፋ በወቅቱ በስልጣን ላይ በነበረው የአካባቢው መስተዳድር የጸጥታ መዋቅርና ሳምሪ በተባለ ኢ-መደበኛ የወጣቶች ቡድን መፈጸሙን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡፡
ይህ ጥቃት፤ ግድያ፣ ጉዳትና ውድመት፤ ጠቅላላ ድርጊቱና ውጤቱ ግፍና ጭካኔ የተሞላበት በበንጹሃን ላይ የተፈጸመ የጭፍጨፋ ወንጀል መሆኑንም ነው ኮሚሽኑ የገለጸው፡፡
ኮሚሽኑ ይህን የገለጸው ከሕዳር 5 እስከ 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በማይካድራ ከተማ፣ በአብርሀጅራ፣ በሳንጃ፣ በዳንሻ፣ በሁመራ እና በጎንደር ከተሞች ተዘዋውሮ ባደረገው ምርመራ የደረሰበትን ግኝት ይፋ ባደረገበት የመጀመሪያ ደረጃ ቀዳሚ ሪፖርት ላይ ነው፡፡
ይህ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል እና የጦር ወንጀል ሊሆን እንደሚችል የሚያመለክት ስለሆነ ኮሚሽኑ ዝርዝር ማስረጃዎቹን እና ወንጀሉን የሚያቋቁሙትን የሕግና የፍሬ ነገር ትንተና በሙሉ ሪፖርቱ ላይ በዝርዝር አጣርቶ እንደሚያቀርብ አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ በቀዳሚ ሪፖርቱ እንዳመለከተው በአካባቢው የነበረው የሚሊሽያና የፖሊስ ጸጥታ መዋቅር በፌዴራሉ አገር መከላከያ ሰራዊት እርምጃ ሸሽቶ አካባቢውን ለቅቆ ከመውጣቱ በፊት ሳምሪ ከተባለ መደበኛ ካልሆነ የትግራይ ወጣቶች ቡድን ጋር በማበርና በመተባበር ጭፍጨፋውን ማካሄዱን ገልጿል፡፡
እነዚህ አካላት “አማሮችና ወልቃይቴዎች” ያሏቸውን የአካባቢው ነዋሪ ሲቪል ሰዎች ቤት ለቤት እየዞሩና በየጐዳናው ላይ በገመድ በማነቅ፣ በስለት በመጥረቢያ፣ በዱላ በመደብደብ መግደላችንና የአካል ጉዳት ማድረሳቸውን ብሎም ንብረት ማውደማቸውን ኢሰመኮ ገልጿል፡፡
ተቋሙ ከአካባቢው ምንጮች እስከ አሁን አገኘሁት ባለው መረጃ በአነስተኛ ግምት እስከ 600 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ትክክለኛው ቁጥር ከዚህ ሊበልጥም እንደሚችል አስታውቋል፡፡
ሳምሪ የተባለው የትግራይ ወጣቶች ቡድን በዚህ ከባድ ወንጀል ላይ ቢሰማራም፤ በአንጻሩ የትግራይ ብሔር ተወላጅች የሆኑ ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች አጥቂው ቡድን ሲያሳድዳቸው የነበሩ ሲቪል ሰዎችን በቤታቸው፣ በቤተክርስቲያን እና በእርሻ ቦታ ደብቀው በመሸሸግ ሕይወታቸውን እንዳተረፉላቸው ኢሰመኮ በሪፖርቱ አካቷል፡፡
የኢሰመኮ ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የተጐዱ ሰዎችን እና አካባቢዎችን መልሶ ከማቋቋምና ከመጠገን በተጨማሪ፤ በዚህ ከባድ የሰብዓዊ መብቶች ወንጀል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የተሳተፉ በየደረጃው ያሉ ጥፋተኞችን በሕግ ፊት ተጠያቂነት ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡