ህግ ማስከበር ዘመቻው ተጠናቋል መባሉን ተከትሎ ኢትዮጵያውያን ደስታቸውን እየገለጹ ነው
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የትግራይ ህዝብ ወንጀለኞቹን ከተደበቁበት እንዲያጋልጥ ጥሪ አቅርበዋል
“በመጪው ጊዜ ደግሞ ትልቅ ሥራ እንደሚጠብቀን ለአፍታም ቢሆን አንዘናጋ”-ሣህለ ወርቅ ዘውዴ
ኢትዮጵያውያን የህግ ማስከበር ዘመቻው ተጠናቋል መባሉን ተከትሎ ደስታቸውን እየገለጹ ነው
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የህወሓት የመጨረሻ ጠንካራ ይዞታ የነበረችውን መቀሌን እንደተቆጣጠረ ማስታወቁን ተከትሎ ኢትዮጵያውያን ደስታቸውን እየገለጹ ነው፡፡
በጎንደር፣ በባህር ዳር እና በሌሎችም የአማራ ክልል ከተሞች በአዲስ አበባ ጭምር ወደ ጎዳናዎች ወጥተው ደስታቸውን የገለጹ፤ ለሃገር መከላከያ ሰራዊቱ እና ለልዩ ኃይል አባላት ምስጋናቸውን የቸሩ በርካቶች ናቸው፡፡
የመንግስት ተቋማት እና ከፍተኛ የሃገር መሪዎችም እንዲሁ በድሉ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንኳን ደስ አላችሁ ሲል በድሉ የተሰማውን ደስታ ገልጿል፡፡ የትግራይ ሕዝብ ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን በመቆም ላሳየው ሕዝባዊና አገራዊ ወገንተኝነት ያመሰገነም ሲሆን የሰራዊቱ ቁርጠኝነትና ተጋድሎ የህግ የበላይነትንና ፍትህን ለማረጋገጥ ወሳኝ ስለመሆኑ ገልጿል፡፡
የቡድኑን አባላት ለፍርድ ለማቅረብ በሚደረገው ቀጣይ እርምጃ ከሠራዊቱ ጎን እንደሚቆም ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ደስታውን የገለጸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ድሉ የመላው ኢትዮጵያውያን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ነው ሲል ገልጿል ባወጣው መግለጫ።
ደስታውንና ድሉን እያጣጣምን የፌዴራል ስርዓቱን የሚሸረሽሩ እኩይ ተግባራትን በተመሳሳይ መልኩ በጋራ እንከላከል ብሏል ምክር ቤቱ፡፡
ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው ህግ የማስከበሩ ምዕራፍ በድል ተጠናቋል፤ በመጪው ጊዜ ደግሞ ትልቅ ሥራ እንደሚጠብቀን ለአፍታም አንዘናጋ የሚል መልዕክትን አስተላልፈዋል፡፡
ድሉ ለሀገራችን ልማትና እድገት ትልቅ መሠረት የሚጥል ነው ያሉት ፕሬዝዳንቷ እጅ ለእጅ ተያይዘን ጠንክረን እንስራም ብለዋል፡፡
በድሉ ጀግና ያሉትን ሰራዊቱን፣ የአማራ ክልል ልዩ ሃይልን እና ሚሊሻዎች አመስግነው እንኳን ደስ አላችሁ የሚል መልዕክትን ያስተላለፉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን “የጁንታውን ቡድን አድኖ ለህግ የማቅረብ ተልዕኮ እስከመጨረሻዋ ሰዓት ተጠናክሮ” እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡
በትግራይ ክልል እና በአካባቢው ፍፁም ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን አስፈላጊውን ከማድረግ በተጨማሪ “ቡድኑ ያፈራረሳቸውን መሰረተ ልማቶች መልሶ የመገንባት እና የማቋቋም ስራዎች” በትኩረት እንደሚከናወኑም ነው አቶ ደመቀ የገለጹት፡፡
የክልሉ ህዝብ ወንጀለኞቹን ከተደበቁበት እንዲያጋልጥም ጥሪ አቅርበዋል።
የተለያዩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በድሉ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡ ከነዚህ ፓርቲዎች መካከልም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) አንዱ ነው፡፡
“የትሕነግ መደምሰስ ለአገራችን ፋይዳው ዘርፈብዙ ነው ነው ያለው አብን ቀሪው ጉዳይ የተከላቸውን የጥላቻ ትርክት፣ ሕገ-መንግስትና መዋቅሮችን በማፈራረስ በአገራችን ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣ ፍትኅ፣ እኩልነትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ማስፈን ነው” ሲል አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ድሉ “የትግራይን ህዝብ ለዘመናት ከተጫነበት ቀንበር የሚያላቅቅ” ነው ብሏል፡፡
“ባለፉት ሳምንታት በህወሓት መራሹ አጥፊ ቡድን እንደ ሰብአዊ ጋሻ ተይዞ የነበረውን የትግራይ ህዝብ” ነጻ የሚያወጣ ድል እንደሆነም ነው ያስታወቀው፡፡
ድሉ ዘላቂና አስተማሪ የሚሆነው“አገር በማፍረስ ተግባር ላይ የተሳተፉ፤ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን እንዲሁም በዜጎቻችን ላይ የደረሰውን ዘግናኝ ጭፍጨፋ ያቀዱ፣ ያስተባበሩና የፈፀሙ አካላት ሁሉ ሕግ ፊት ቀርበው ተገቢውን ቅጣት ሲያገኙ” እንደሆነም ነው ኢዜማ ያሳሰበው፡፡
መንግስት ካለፈው በመማር “የፖለቲካ ፍላጎትን በሃይል ለመጫን የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ ሕጋዊ የሆነ እርምጃ በመውሰድ ኃላፊነቱን በቁርጠኝነት እንዲወጣ”ም ጠይቋል።