የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በታሪኩ ከፍተኛ ነው ያለውን 25.6 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን ገለጸ
ባንኩ በበጀት ዓመቱ 135.4 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ማግኘቱንም አስታውቋል
የባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ1.17 ትሪሊዮን የተሻገረ ሲሆን የደንበኞቹ ቁጥር ከ45 ሚሊዮን በላይ ሆኗል
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበጀት ዓመቱ በባንኩ ታሪክ ከፍተኛ የሆነውን 25.6 ቢሊዮን ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ።
ባንኩ በ2023/24 ወይም የ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን በማህበራዊ ትስስር ገጹ ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ በበጀት ዓመቱ ስኬት ማስመዝገቡን ገልጿል።
በበጀት ዓመቱ 135.4 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ማግኘቱን የጠቆመው ባንኩ፣ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ13 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ነው የገለጸው።
ባንኩ ከታክስ በፊት ያገኘው 25.6 ቢሊዮን ብር ትርፍም በታሪኩ ከፍተኛው ሆኖ መመዝገቡን ነው ያነሳው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ1.17 ትሪሊዮን ብር መሻሩን ያስታወቀ ሲሆን፤ የደንበኞቹ ቁጥር ከ45 ሚሊዮን በላይ ደመድረሱንም ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
ከብድር አቅርቦት ጋር በተያያዘም ባንኩ በበጀት ዓመቱከ218 ቢሊዮን ብር በላይ የብድር አገልግሎት ማቅረቡንና ከዚህም ውስጥ 91 በመቶ ወይም ከ198 ቢሊዮን ብር በላዩ ለግሉ ዘርፍ የተለቀቀ መሆኑንም አብራርቷል።
በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ በቁጥር ከ1.56 ቢሊዮን የሚበልጥ ግብይት፤ ወይም በገንዘብ ከብር 31.6 ትሪሊዮን በላይ የገንዘብ ዝውውር ሲፈፀም፤ ከዚህ ውስጥ በቁጥር ከ1.19 ቢሊዮን ወይም 72% የሚሆነው ግብይት በዲጂታል የክፍያ አማራጮች የተከናወነ መሆኑን ባንኩ አስታውቋል።
በሌላ በኩል ከሲስተም ማሻሻያ ጋር በተገናኘ መጋቢት 7 ቀን 2016 ዓ.ም በተፈጠረ ችግር ምክንያት ያለአግባብ ተወስዶ ከነበረው ብር 801.4 ሚሊዮን ገንዘብ ውስጥ 99.34% ወይም ብር 796.6 ሚሊዮን የሚሆነውን ማስመለስ የተቻለ ሲሆን ቀሪውን 4.76 ሚሊዮን ብር ለማስመለስ ጥረቶች መቀጠላቸውንም ባንኩ ገልጿል።