ኮሚሽኑ ለሰብአዊ እርዳታ የሚውል እህል ለማምረት 250ሺ ሄክታር እያለማ መሆኑን ገለጸ
የኢትዮጵ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ሰበአዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን እየሰራሁ ነው ብሏል
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ድጋፍ የሚያሻቸውን ሰዎች ለመድስ 20 ሚሊዮን ኩንታል እንደሚያስፈልገው ኮሚሽኑ ገልጿል
ኮሚሽኑ ለሰብአዊ እርዳታ የሚውል እህል ለማምረት 250ሺ ሄክታር እያለማ መሆኑን ገለጸ።
የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከተለያዩ የረድኤት ድርጅቶች የሚያገኝውን የሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም ለመሸፈን ወደ እርሻ ስራ መግባቱን ገልጿል።
በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሯዊ ምክንያቶች የተለያየ ጉዳት ደርሶባቸው እርዳታ የሚያሻቸውን ዜጎች ለመድረስ የአልሚ ምግቦችን ጨምሮ እህል እና የተለያዩ ቁሳቁሶች ኮሚሽኑ ከረጂ አካላት ድጋፍ እንደሚደረግለት ይታወቃል፡፡
በዚህም በተለይ በእህል እርዳታ በኩል ያለውን የውጭ ጥገኝነት ለማስቀረት እና በራስ አቅም ለመሸፈን ኮሚሽኑ የራሱን ምርት ወደ ማምረት እንቅስቃሴ መግባቱን አል ዐይን አማረኛ ከኮሚሽኑ ያገኝው መረጃ ይጠቁማል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ በተለያዩ ምክንያቶች ድጋፍ የሚያሻቸውን ዜጎች ለመድረስ የሚያስፈልገው የምርት መጠን በመጠባበቂያ ክምችት ደረጃ አምስት ሚሊዮን ኩንታልና አስቸኳይ የዕለት ደራሽ 15 ሚሊዮን በአጠቃላይ 20 ሚሊዮን ኩንታል ነው፡፡
ኮሚሽኑ በራስ አቅም ምርትን ለመሸፈን እያደረኩት ነው ባለው ጥረት 500 ሺህ ኩንታል መጠባበቂያ እና 1.5 ሚሊየን ኩንታል የዕለት ደራሽ ለማከማቸት አቅዶ እየሰራ እንደሆነ ታውቋል፡፡
ይህን በሁሉም ክልሎች ተገባራዊ ሲደረግ 99 በመቶ ምርትን በራስ ለመሸፈን የሚያስችል መሆኑ ተነግሯል፡፡
የኮሚሽኑ ጊዜያዊ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሚኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ አቶ አታለል አቧሀይ ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት ካሳለፍነው አመት ሰኔ ወር ጀምሮ በርካታ ክልሎች ይህን ተግባራዊ ወደ ማድረግ ገብተዋል፡፡
በተለይም የአማራ ፣ ኦሮሚያ ፣ ሶማሊያ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽኖች በስፋት እየተንቀሳቀሱ ከሚገኙት መካከል ተጠቃሽ ናቸው ተብሏል፡፡
የህዝብ ግንኙነት ስራ አስፈጻሚው አክለውም የክልል ኮሚሽኖች ምርት ማምረት ፣ መሰብሰብ እና ማከማቸት የሚችሉበትን አቅም እንዲያያዳብሩ እንዲሁም የእህል ማከማቻ መካዘኖችን እንዲገነቡ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
በቀጣይ የትኛው ክልል ምን አይነት ምርት በምን ያህል መጠን አመረተ የሚለውን ኮሚሽኑ ይፋ አደርጋለሁ ብሏል፡፡
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በአሁኑ ወቅትም ለዚሁ ዓላማ እንዲውል በ50 ሄክታር መሬት ላይ በበቆሎ ተዘርቶ እየለማ መሆኑን የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር ለማ መሰለ (ዶ/ር) ባሳለፍነው አመት ሀምሌ ወር ላይ ተናግረው ነበር።
የሚመረተውን ምርት ሰብስቦ ለማከማቸት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ ለቁሳቁስ ግዥም 9 ሚሊዮን ብር ተመድቧል ነው ያሉት፡፡
አዲስ አበባና ድሬዳዋ አስተዳደሮችን ጨምሮ ስድስት ክልሎች በአሁን ጊዜ ምንም አይነት ሰብዓዊ ድጋፍ ከፌዴራል መንግስት ሳይወስዱ ሰብአዊ ድጋፎችን በራሳቸው እያሰራጩ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ባለፈው በጀት አመት ማጠናቀቂያ ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራርያ በ2016 በጀት ዓመት ብቻ ምግብ ነክ ሰብአዊ ድጋፎችን ገዝቶ ለማከፋፈል ከ47 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን አመላክተዋል፡፡
ሰብአዊ ድጋፎችን በራስ አቅም ለመሸፈን የሚደረገው ጥረት አካል ነው በተባለው እንቅስቃሴ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 5.1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስንዴ በመግዛት ለ6.5 ሚሊየን ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ መቻሉንም ነው ያብራሩት።
ኮሚሽኑ በራሱ አቅም የሰብአዊ ድጋፍ ምርቶችን ለመሸፈን እየሰራው ያለው ስራ በውጭ የረድኤት ተቋማት ላይ ያለውን ጥገኝነት ምን ያህል ይቀንሰዋል የሚለው ጥያቄ አቶ አታለል ሲመልሱ “ከሰብአዊ ድጋፍ ጋር በተገናኝ ኮሚሽኑ የሚከተለው መንግስት መር ፖሊሲ ነው፤ ከዚህ አንጻር በውጭ አካላት ጋር ያለንን ጥገኝነት ለመቀነስ ከምናደርገው እንቅስቃሴ እንዱ አስፈላጊ የእህል ምርቶችን ሙሉ ለሙሉ መሸፈንን ይመለከታል፤እርሱ በሂደት ሲሳካ የእርዳታ ድርጅቶች የሚኖራቸው ሚና ስንዴ መላክ ሳይሆን የአደጋ ቅነሳ ላይ ፣ ዜጎች እራሳቸውን እንዲችሉ በሚያስችሉ ፕሮጀክቶች እና የልማት ስራዎች ላይ ድጋፍ ማድረግ ላይ እንዲያተኩሩ ይደረጋል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ለ20 አመታት በእርዳታ ኑሯቸውን የሚገፉ ሰዎች እንዳሉ የሚናገሩት አቶ አታለል እርዳታ የሰውን ህይወት የማይቀይር በመሆኑ በቀጣይ በቋሚነት የሚረዱ ሰዎችን ህይወት ለማሻሻል የሚያግዙ ፕሮጀክቶችን ወደ ተግባር ለማስገባት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ምን ያህል ድጋፍ የሚያስፈልገው የተረጂ ቁጥር አለ ስንል የጠየቅናቸው የኮምኒኬሽን ስራ አስፈጻሚው ቁጥሩ በየጊዜው ስለሚቀያየር አሁን ላይ ትክክለኛው መረጃ የለኝም ሲሉ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
በሌላ በኩል ኮሚሽኑ ትክክለኛ የተረጂዎች ቁጥርን ለማወቅ እና ወደ ዲጂታላይዝድ ለመቀየር “የማህበራዊ መመዝገቢያ ስርአት” የተባለ አሰራር በሙከራ ደረጃ በሀረሪ ክልል ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
አቶ አታለል“ኦፕን ጂቱፒ” ከተባለ ተቋም ጋር እየተሰራበት የሚገኝው ምዝገባ ተረጂዎች የዲጂታል መታወቂያ እንዲኖራቸው በማስቻል ትክክለኛውን የሰብአዊ ድጋፍ ተጠቃሚ ቁጥር ለማወቅ እና ድግግሞሽን ለማስቀረት ይረዳል ብለዋል፡፡